
በሀረሪ ክልል ሀረር ከተማ ኡምራ ጃተኒ የተባለ አካባቢ ላይ አቶ ሙፍቱ የሱፍ የተባሉ ግለሰብን በቅንጅት የገደሉ ሰባት ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ጽ/ቤት አስታውቋል።
ከዚህ በፊት በመካከላቸው የነበረውን ጸብ እና ቂም በመያዝ ድርጊቱን መፈጸማቸውን የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ ዓቃቢ ህግ እጸገነት ሃይሉ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል። አንደኛ ተከሳሽ ፉዓድ አቡበከር የተባለው ግለሰብ ሲሆን ሜንጫ በተባለ ስለት የግል ተበዳይ ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት አድርሷል። የግል ተበዳይ መሬት ላይ ሲወድቅ ሁለተኛ ተከሳሽ ደጋግሞ በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርገዋል።
በተጨማሪም ከሶስተኛ እስከ ሰባተኛ የተከሰሱ ግለሰቦች የማች አቶ የሱፍ ኢብራሂምን አስከሬን አንስተው በድብቅ ስፍራ ቀብረዋል። አያይዘውም የሟችን ቤት በማፈራረስ ከጥቅም ውጪ አድርገዋል ።
ሰባቱ ግለሰቦች የሰው ህይወት በማጥፋት እና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ በፖሊስ የምርመራ መዝገባቸው ተጣርቷል ። ዓቃቢ ህግምየተላከለትን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ክስ መስርቷል።
በዚህም መሰረት የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ ፉዓድ አቡበከር ሁለተኛ ተከሳሽ ከድር እስማዔል እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት እስራት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
ሌሎች ከሶስተኛ እስከ ሰባት ያሉት ተከሳሾች በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ጽ/ቤት ሃላፊ ዓቃቢ ህግ እጸገነት ሃይሉ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በኤደን ሽመልስ