መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 1፤2016 – ኬንያ ከኩባ ዶክተሮች ጋር ያለውን ስምምነት ልታቆም ነው

ኬንያ ከ100 የሚበልጡ የኩባ ዶክተሮች በኬንያ ሆስፒታሎች እንዲሰሩ የፈቀደችውን የስድስት አመት ስምምነት ልታቋርጥ መሆኑን አስታውቃለች። የኬንያ የጤና ሚኒስትር ሱዛን ናኩሚቻ እንደተናገሩት እርምጃው በኬንያ የጤና ሰራተኞች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ይረዳል፣ ይህም የስራ እድሎችን ለኬንያውያን ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።

“ከኩባ ዶክተሮች ጋር ያለውን ስምምነት ላለማደስ ወስነናል። የራሳችን የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ለጉዳዩ ቁርጠኞች ናቸው፤›› ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። በ2017ቱ ስምምነት መሰረት የኩባ ዶክተሮች በኬንያ ሆስፒታሎች ያለውን ክፍተት ለመሙላት ሲረዱ ኬንያውያን ለልዩ የህክምና ስልጠና ወደ ኩባ የሚሄዱበት የልውውጥ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

የሃገር ውስጥ ዶክተሮች ልክ እንደ ኩባ አቻዎቻቸው አስፈላጊውን ስልጠና ወስደዋል ብለው የሚከራከሩት የኬንያ የህክምና ባለሙያዎች ስምምነቱን ሲቃወሙ ቆይተዋል።በተጨማሪም የኬንያ መንግስት ለኩባ ባለሙያዎች ከኬንያ አቻዎቻቸው እጅግ የሚበልጥ ክፍያ እየከፈላቸው ነው የሚለው ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል።በአገር ውስጥ የሰለጠኑ አንዳንድ ዶክተሮች ሥራ አጥ ሆነው መቅረታቸው አሳዛኝ እውነታ ያደርገዋል።

በኬንያ የሚገኙ ዶክተሮች እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ደመወዝ እንዲጨምር፣ የተሻለ የስራ ሁኔታ እንዲፈጠር እና በርካታ ዶክተሮች እንዲቀጠሩ በመጠየቅ የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *