በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በገደር ከተማ 01 ቀበሌ የአክስቱን ልጅ የሆነችውም የ12 ዓመቷን ታዳጊ በመድፈር የተከሰሰው ግለሰብ በእስራት መቀጣቱን የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ፖሊስ የኮምኒኬሽን ጉዳይ ፅ/ቤት ገልጿል።
የምስራቅ ሀረርጌ ፖሊስ መምሪያ የኮምኒኬሽን ጉዳይ ፅ/ ቤት ሃላፊ ም/ኮማንደር ቶሎሳ ጎሾ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት በቀለ ሚሊዮን የተባለው ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን ገልፀዋል።
ተከሳሹ በገደር ከተማ 01 ቀበሌ ውስጥ የ6ተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው የአክስቱን ልጅ ከትምህርት ቤት ስትመለስ ትምህርት ቤት በር ላይ በመጠበቅ ወደ መኖሪያ ቤቱ በመውሰድ ነው የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደፈፀመባት ፖሊስ ያስታወቀው።
ተከሳሹ ድርጊቱን ከፈፀመ በኃላ የ12 ዓመቷ ልጅ የተፈፀመባትን ድርጊት ለወላጆቿ ከተናገረች እንደሚገላት በማስፈራራት ወደ ወላጆቿ ይሸኛታል። በማግስቱ ግን ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ሲያቅታት ወላጆቿ የደረሰባትን ጉዳት መረዳት በመቻላቸው ጉዳዩ ለፖሊስ ሊያሳውቁ ችለዋል።
ፖሊስም ተከሳሹን ክትትል ሲያደርግበት ከሚኖርበት ገደር 01 ቀበሌ ተሰውሮ ወደ ሀረር ከተማ ሊያመልጥ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል።
የምርመራ መዝገቡም በህክምና እና በተጎጂዋ ማስረጃ ተጣርቶ ለዓቃቢ ህግ የተላከ ሲሆን ዓቃቢ ህግም የተላከለትን መዝገብ ተመልክቶ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች እና በቅርብ ዘመዳሞች ላይ የሚፈፀም የመደፈር ወንጀል በመጥቀስ ለምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ይከፍታል።
ፍርድ ቤቱም የቀረበለትን የክስ መዝገብ ሲመረምር ቆይቶ ተከሳሽ በቀለ ሚሊዮን በ21 ዓመት እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።
በምህረት ታደሰ