መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 5፤2016 – በአዲስ አበባ ኮዬ ፈጩ በደረሰ የእሳት አደጋ አምስት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደሙ

በትላንትናው እለት ጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 6:47 ገደማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ኮየ ፈጩ አካባቢ በተነሳ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ውድመት ሲደርስ በአንድ ሰዉ ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በእሳት አደጋዉ አንድ ጋራዥ ከአምስት ተሽከርካሪዎች ጋር ፣ የብየዳ አገልግሎት መስጫ፣ጎሚስታና ግሮሰሪ ተቃጥለዋል።

በጋራዡ ለጥገና የገቡ ተሽከርካሪዎች ዉስጥ የነበረ ነዳጅ እና ሌሎች ፈሳሽ ተቀጣጣዮች መኖራቸዉ እንዲሁም ጥሪዉ ዘግይቶ መድረሱ ለእሳት አደጋዉ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተነግሯል።

የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እሳቱ ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በዚህ ሂደት 32 ከብቶችንና  ከፍተኛ ግምት ያለዉ እህል እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችን ማዳን ስለመቻሉ አቶ ንጋቱ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።

የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ዘጠኝ የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪና አንድ የዉሀ ቦታ ከሀምሳ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር የተሰማራ ሲሆን የእሳት አደጋዉን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ሁለት ሰዓት ፈጅቷል።

የእሳት አደጋዉን በመቆጣጠር ስራ ላይ ከነበሩት ባለሞያዎች መካከል በአንድ የአደጋ መቆጣጠር ሰራተኛ ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።በሌላ በኩል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በግተራ እየተባለ በሚጠራዉ አካባቢ ቅዳሜ ረፋድ 4:52 ሰዓት በተነሳ የእሳት አደጋ አንድ የመኖሪያ ቤት ሲቃጠል በሁለት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *