መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 5፤2016 – ከ3 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት በህገወጥ መንገድ አከማችተው የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

በምስራቅ ወለጋ ዞን በህገወጥ መንገድ የምግብ ዘይት በመጋዘን ያከማቹ እና በድብቅ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን  በምስራቅ ወለጋ ፖሊስ የኮሙኒኬሽን ጽ /ቤት ሃላፊ  የኔነሽ አለሙ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።

አንደኛ ተከሳሽ በላይ ሻንቆ ሁለተኛ ተከሳሽ ናስር አህመድ የተባሉት ተከሳሾች ባለ ሁለት ሊትር ብዛቱ 150 የሆነ 3ሺህ ሊትር ዘይት  ፣ ባለ አምስት ሊትር ብዛቱ 90 የሆነ እና ባለ አንድ ሊትር ስልሳ ካርቶን የምግብ ዘይት በአጠቃላይ ሶስት ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ ስድስት ሊትር ዘይት በቁጥጥር  ስር ውሏል።

ዘይቱን በመጋዘን ካከማቹ በኋላ ጨለማን ተገን አድርገው ከነቀምት  ወደ አንደርጉቱ ከተማ ለማጓጓዝ  ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል።  ሁለቱም ግለሰቦች  በቁጥጥር  ስር ከዋሉ በኋላ ወንጀል ድርጊቱ በምርመራ  ተረጋግጧል።በዚህም የወንጀል  መዝገቡ ለዓቃቢህግ ተልኳል።

ዓቃቢህግ በህገወጥ የወንጀል ድርጊት  እና ለምግብ ፍጆታ የሚውል ምርትን በህገወጥ መንገድ በማከማቸት እና በማዘዋወር ክስ ከፍቷል።

ክሱን ሲመለከት የነበረው የምስራቅ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለቱን ተከሳሾች ጥፋተኛ በማለት እያንዳንዳቸው በሰባት ዓመት እስራት እና 200ሺህ ብር  የገንዘብ ቅጣት የተላለባቸው መሆኑን ኢንስፔክተር የኔነሽ ዓለሙ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *