መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 6፤2016 – እስራኤል በአንድ ሌሊት በፈፀመችው የአየር ጥቃት 80 ሰዎች ተገደሉ

በራፋህ እና በካን ዮኒስ 3 የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ እስራኤል በፈፀመችው የአየር ጥቃት በአንድ ሌሊት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 80 ከፍ ብሏል።እስራኤል ሲቪሎች እንዲጠለሉ ባዘዘችባቸው ካን ዮኒስ፣ ራፋህ እና ዴይር ኤል-ባላ ውስጥ በሦስት አካባቢዎች በጣም ከባድ የሆነ የቦምብ ድብደባ ፈፅማለች።

በራፋህ እና በካን ዮኒስ መኖሪያ ቤቶች ላይ በደረሰው የቦምብ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ የህክምና ምንጮች ተናግረዋ። ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ተጨናነቁ ሆስፒታሎች አምቡላንሶች እያጓጓዙ ሲሆን አሁንም በርካታ ሰዎች በፍርስራሹ ውስጥ ይገኛሉ።

የእስራኤል ፖሊስ በበኩሉ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 5 መኮንኖች መገደላቸውን ተናግሯል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጋዛ በሚገኙ የሃማስ ታጣቂዎች ላይ የምድር ጥቃት ለመሰንዘር የተያዘውን እቅድ ለመወያየት በነገው እለት እስራኤልን ይጎበኛሉ። ባይደን እስራኤል እንዴት በሲቪል ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በቀነሰ መልኩ ዘመቻውን ማካሄድ እንደምትችል ይመክራሉ።

ሃማስን የምትደግፈው ኢራን በሰጠችው ጠንካራ ማስጠንቀቂያ በሚቀጥሉት ሰዓታት በእስራኤል ላይ “ቅድመ መከላከል እርምጃ” ልትወስድ እንደምትችል ተናግራለች። ይህ ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በኢራን የሚደገፈውን የሂዝቦላህ ሚሊሻን ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል። ቡድኑ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከእስራኤል ጋር የተኩስ ልውውጥ እያደረገ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግስታቱ ድርጅት የእርዳታ ሃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ በሃማስ በሚመራው የጋዛ ሰርጥ የጤና ስርዓቱ እና ሆስፒታሎች እየፈራረሱ ነው ብሏል ። የፍልስጤም ባለስልጣናት እስራኤል ሰኞ ምሽት በራፋህ ድንበር ማቋረጫ አቅራቢያ ጨምሮ በደቡባዊ ጋዛ ላይ ባደረሰችው ጥቃት 49 ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል። ከጥቅምት 7 ጀምሮ በእስራኤል ውስጥ ከ 1,300 በላይ ሰዎች በሃማስ ተገድለዋል። እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው የአጸፋ ጥቃት ከ2,700 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *