መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 7፤2016 – የዮርዳኖስ ንጉስ አብዱላሂ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር የነበራቸውን ስብሰባ ሰርዘዋል

በጋዛ ሆስፒታል ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ዮርዳኖስ ከባይደን ጋር የነበረውን ስብሰባ ሰርዛለች።ዮርዳኖስ በዛሬው እለት በአማን ከተማ ልታስተናግደው የነበረው ስብሰባ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፣ ከግብፅ እና ከፍልስጤም መሪዎች ጋር በጋዛ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ታቅዶ የነበረውን ስብሰባ መሰረዟን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ተናግረዋል።

ሳፋዲ እንደተናገሩት ስብሰባው የሚካሄደው ሁሉም አካላት “ጦርነቱን እና ፍልስጤማውያን ላይ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ” ለማስቆም በሚስማሙበት ጉዳይ ነው። እስራኤል በወታደራዊ ዘመቻዋ ክልሉን ወደ “ጥልቁ አፋፍ” ለመግፋት ወስናለች።ባይደን ወደ እስራኤል ከሚያደርጉት ጉዞ በኃላ ወደ ዮርዳኖስ ያቀናሉ ከዛም የግብፁን ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲን እና የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን ያገኛሉ ተብሎ የወጣው የጉዞ መርሃ ግብር ያሳያል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ወደ ዮርዳኖስ እንዳይመጡ ስብሰባው በመሰረዙ እስራኤልን ብቻ ይጎበኛሉ፤ ወደ ዮርዳኖስ የሚያደርጉትን ጉዞ ለሌላ ጊዜ እንደሚተላለፍ የዋይት ሀውስ ባለስልጣናት ተናግረዋል ። አብዱላህ በትላንትናው እለት 500 የሚጠጉ ፍልስጤማውያንን ለገደለው የጋዛ ሆስፒታል ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ በማድረግ “በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ አሳፋሪ ክስተት” በማለት እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ጥቃት በአስቸኳይ እንድታቆም ጠይቀዋል።

የፍልስጤም ባለስልጣናት ፍንዳታው የተከሰተው በእስራኤል የአየር ጥቃት ነው ብለዋል። የእስራኤል ባለስልጣናት ፍንዳታው የተከሰተው በፍልስጤም የታጠቀ ቡድን የተወነጨፈ ሮኬት በተሳሳተ መንገድ በመተኮሱ ነው ብለዋል።ንጉስ አብዱላህ  በሃማስ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል የአፀፋ ምላሽ እራስን የመከላከል መብት ከማስከበር ባለፈ የፍልስጤም ሲቪሎችን በጋራ የመቀጣት ሂደት ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ንጉስ አብዱላሂ ከባይደን ጋር የነበራቸውን ስብሰባ መሰረዛቸው የአሜሪካን ተፅእኖ በገደብ የሚፈተሽበት መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል።ከአባስ ወይም ከማንኛውም የፍልስጤም ባለስልጣን ጋር መገናኘት አለመቻል፣ የባይደን ዲፕሎማሲያዊ መልእክት ሊያዳክም እና በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ትችት ሊያስከትልባቸው ይችላል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *