
በደቡባዊ ሞዛምቢክ የወፍ ጉንፋንን ለመከላከል ከ45 ሺ የሚበልጡ ዶሮዎች ታርደው እንዲቃጠሉ እና እንዲቀበሩ መደረጉን የመንግስት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ወፎቹ በበሽታው ከተጠቁ ከጎረቤት ደቡብ አፍሪካ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ናቸው ። ወረርሽኙ በአሁኑ ወቅት በደቡባዊ ኢንሃምበን ግዛት ውስጥ ወደምትገኘው የሞዛምቢክ አውራጃ ሞሩምቤኔ ተዛምቷል። ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ባለስልጣናት ለመቆጣጠር እየሞከሩ ይገኛል።
የወፍ ጉንፋን የዶሮ እና የዱር አእዋፍ ተላላፊ በሽታ ነው።በጥቂት ቀናት ውስጥ በሽታው በአእዋፋት መንጋ በፍሳሽ እና ምራቅ ወይም በተበከለ መኖ እንዲሁም ውሃ ሊሰራጭ ይችላል። ወረርሽኙ የእንቁላል እና የዶሮ እጥረትን ያስከተለ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በሞዛምቢክ ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ዋና ከተማዋን ማፑቶንን ጨምሮ ተመዝግቧል።
የዶሮ ዋጋ ከ350 የሞዛምቢክ ሜቲካል ወይም 5 አምስት የአሜሪካ ዶላር ወደ 600 የሞዛምቢክ መገበያያ ገንዘብ ሜቲካል ከፍ ብሏል። የዋጋው ጭማሪ በእጥፍ ሊጠጋ የተቃረበ ሲሆን የአንድ ደርዘን እንቁላል ዋጋ ከ100 ወደ 150 ሜቲካል ጭማሪ አሳይቷል።
45 ሺዎቹ የተቃጠሉት ዶሮዎች በደቡብ አፍሪካ በወፍ ጉንፋን ከተያዙ ዶሮዎች ጋር ግንኙነት ነበራቸው ሲሉ የሞዛምቢክ የእንስሳት ሀብት ልማት ብሔራዊ ዳይሬክተር አሜሪኮ ዳ ኮንሴሳኦ ተናግረዋል። ዶሮዎቹ እንቁላል ጣይ ሲሆኑ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ሞዛምቢክ የመጡ አሉበት። ደቡብ አፍሪካ ከከፋ የወፍ ጉንፋን ወረርሽኝ ጋር ስትታገል ቆይታለች።
ይህው በሽታ የዶሮ እርባታ ገበሬዎች ሰባት ሚሊዮን እንቁላል የሚጥሉ ዶሮዎችን እንዲገድሉ ያስገደዳቸው ሲሆን ከአገሪቱ አጠቃላይ የዶሮ ክምችት ከ 20 እስከ 30 በመቶ ድርሻ እንዳለው የደቡብ አፍሪካ የዶሮ እርባታ ማህበር አስታውቋል። ወረርሽኙ በሀገሪቱ የእንቁላል እና የዶሮ ሥጋ አቅርቦት ላይ እጥረት ፈጥሯል።
ዳ ኮንሴካዎ እንዳሉት ሞዛምቢክ ዶሮ፣ እንቁላል እና የዶሮ መኖን ጨምሮ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ አግዳለች። የወረርሽኙ ማዕከል ከሆነችው ሞርምቤን ወደ ሌሎች የሞዛምቢክ አካባቢዎች የሚደረገውን የዶሮ፣የእንቁላል እና የእንስሳት መኖ ንግድ መንግስት አቁሟል። ባለሥልጣናቱ ዶሮዎቹ የተቃጠሉት ሰዎች ከታረዱ በኋላ እንዳይወስዷቸውና እንዳይበሉ በሚል ነው ብለዋል።
በስምኦን ደረጄ