መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 12፤2016-እስራኤል በጋዛ ጦርነት እንድታቆም ካልሆነ ግን ቀጠናው ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል ስትል ኢራን አስጠነቀቀች

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴን አሚር አብዶላሂን እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ጥቃት ካላቆመች መካከለኛው ምስራቅ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ለእስራኤል ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ ዩናይትድ ስቴትስ ተጠያቂ ናት ብለዋል።

ከኢራን መግለጫ ከሰዓታት በኋላ የእስራኤሉ ጠ/ሚ ቤንያሚን ኔታንያሁ ህዝባችን ለህይወቱ ሲል እየታገለ ነው ሲሉ ለወታደሮቻቸውን ተናግረዋል። ከሃማስ ጋር የሚደረገው ጦርነት “የህይወት ወይም የመሞት ጉዳይ ነው” ብለዋል። ኢራን ጠንካራ የሀማስ እና የሊባኖሱን ሂዝቦላህ ደጋፊ ነች።

ዩናይትድ ስቴትስ እና ተላላኪዋ እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰዱት ያለው እርምጃ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጥፋት ወንጀል በአስቸኳይ ካላቆሙ በማንኛውም ጊዜ ማንኛውም ነገር ሊከሰት ይቻላል እንዲሁም ቀጠናው ከቁጥጥር ውጭ እንደሚሆን አስጠንቅቄያለሁ ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል። ቴህራን ውጤቱ በቀጠናውም ሆነ ጦርነቱ ለሚፈልጉት አካላት “ከባድ፣ መራራ” እና “ብዙ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል” ብላለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለው አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ በጋዛ እየተካሄደ ያለው ግጭት “በእስራኤል ዩናይትድ ስቴትስ የውክልና ጦርነት” እያካሄደች ስለመሆኑ ማስረጃ ነው ብለዋል። የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ግጭቱ ሊስፋፋ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ይገኛል። የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን በበኩላቸው በአሜሪካ ወታደሮች ወይም ዜጎች ላይ “ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ሊባባስ” እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በኤቢሲ ኔትወርክ የዚ ሳምንት ፕሮግራም ላይ “ይህን ግጭት ለማስፋፈት እና በአሳዛኝ ሁኔታ ለመጠቀም የትኛውም ቡድን ወይም የትኛውም ሀገር የሚፈልግ ከሆነ ምክራችን ግን አታድርጉት” ነው ሲሉ ተናግረዋል።በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ጥምር ጦር የሚጠቀሙባቸው በርካታ የኢራቅ የጦር ሰፈሮች ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በሮኬት ጥቃቶች ኢላማ ሆነዋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *