መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 13፤2016 – በእስራኤል – ፍልስጤም ጦርነት ከ 20 በላይ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን የእስራኤል ጦር አባላት ተገድለዋል ተባለ

በእስራኤል እና ፍልስጤም ጦርነት ቁጥራቸው ከ 20 በላይ የሆኑ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን የእስራኤል ጦር አባላት ህይወታቸው ማለፉን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከቤተ – እስራኤላውያን ሰምቷል።

ከዚህ ቀደም ቁጥራቸዉ 7 የሆኑ የሀገሪቱ ጦር አባላት የሆኑ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር በተደረጉ ዉጊያዎች መገደላቸዉን ብስራት የዘገበ መሆኑ አይዘነጋም። አሁን ይህ ቁጥር አሻቅቦ እስካሁን መሞታቸዉ የተረጋገጡ 22 የሀገሪቱ ጦር አባላት መታወቃቸዉን የቤተእስራኤላውያን ፅዮናዊያን አክቲቪስት መስፍን አሰፋ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

እስካሁን በእስራኤል መንግስት በኩል የተረጋገጠ መረጃ ይፋ ባይደረግም ፤ በትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ በኩል ግን ህይወታቸውን ላጡ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን የሀዘን መልዕክት እየተላለፈ መሆኑን ገልጸዋል። እስካሁን በእስራኤል ወገን ከ 1 ሺህ 400 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከነዚህ ዉስጥ 300 ገደማዎቹ የሀገሪቱ ጦር እና የጸጥታ ሀይል አባላት ናቸዉ።

በሐማስ ከታገቱ እስራኤላውያን ዉስጥም ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል ያሉን ሲሆን መረጃ በመሰባሰብ ላይ መሆኑንም አንስተዋል።

በጦርነቱ እስካሁን ድረስ ከ 5 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸዉ ሲዘገብ 40 በመቶ ተጎጂዎች ህጻናት መሆናቸዉን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አሳዉቋል። በተጨማሪነትም 1 ሺህ 400 ሰዎች ያሉበት የማይታወቅ ሲሆን ህይወታቸዉ ሳያልፍ እንዳልቀረ ይገመታል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *