መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 15፤2016 – የተለያዩ ወንጀሎችን ፈፅሞ ሲፈለግ የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነገረ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቤንች ሸኮ ዞን በጦር መሳሪያ ንጥቂያ ፣ በዘረፋ እና በሞተር ስርቆት ተግባር  በፖሊስ ሲፈለግ የነበረዉ ተጠርጣሪ ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም በሚዛን አማን ከተማ በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል ።

ተጠርጣሪዉ ቀደም ሲል በደቡብ ቤንች ወረዳ ቂጤ ቀበሌ ከጥበቃ ሰራተኛ ክላሽ መሳሪያ ነጥቆ የተለያዩ የዘረፋ እና የውንብድና ወንጀል ሲፈፅም እንደቆየ ተገልጿል ። ግለሰቡ በነጠቀዉ የጦር መሳሪያውን ከሁለት ግብራበሮቹ ጋር በመንገድ ላይ ዘረፍ ሲፈፅም ተደርሶባቸዉ ሌሎቹ በቁጥጥር ሲዉሉ አምልጦ መቆየቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ። ።

በተጨማሪም ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል ከሚዛን አማን ሰርቆ በመዉሰድ ሞተሩ በመፈታታት በአራት ማዳበሪያ በማድረግ ወደ ሌላ አከባቢ ለመዉሰድ ሲል በዞኑ በደቡብ ቤንች ወረዳ ቂጤ ቀበሌ ኩሪታ መንደር ዉስጥ የሞተሩን አካላት ፣ የእጅ ባትሪ፣ የመከላከያ አልባሳት እና ለዘረፋ ይጠቀምበት የነበረ አርተፊሻል ሽጉጥ በቁጥጥር ስር ሲውል ተጠርጣሪዉ መሠወሩን ተናግረዋል ።

በዚህም መሠረት ፖሊስ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ በሚዛን አማን ከተማ ዉስጥ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ አማካኝነት ግለሰቡን ከ12 ጎራሽ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል ተብሏል ። ፖሊስ ተጠርጣሪዉን ለመያዝ የህብረተሰቡ ትብብር ከፍተኛ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ለተደረገው ትብብር ምስጋናቸዉን አቅርበዋል ።

በአበረ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *