በ2015 የትምህርት ዘመን በዝዋይ እና በቃሊቲ ማረሚያ ማዕከል የሚገኙ 49 የሕግ ታራሚዎች የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አራት ተማሪዎች መንግስት ያስቀመጠውን የማለፊያ ነጥብ አምጥተዋል፡፡አንድ ተፈታኝ ታራሚ ከ600ጠቅላላ ድምር 401 ማምጣቱን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳሬክተር አቶ ገረመው አያሌው ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
በዝዋይ ማረሚያ ማዕከል የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ 30 የሕግ ታራሚዎች መካከል የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ላመጡ ሦስት የሕግ ታራሚዎች ጥቅምት 8 ቀን 2016ዓ.ም. ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ የማለፊያ ውጤት ያመጡ ታራሚዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የነገሩን አቶ ገረመው በአገር አቀፍ ደረጃ ከመጣው ውጤት አንፃር ጥሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የማለፊያ ነጥብ ያመጡ ታራሚዎች ዩኒቨርስቲ ገብተው ወይም በርቀት የሚማሩበትን ሁኔታ እንደሚያመቻችም ተነግሯል፡፡የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ከጎልማሶች ትምህርት ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የቀለም ትምህርት እንደፍላጎታው እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡
በትግስት ላቀዉ