መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 22፤2016- በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እስራኤል በፈፀመችው የቦምብ ጥቃት 200 የሚጠጉ ሰዎች ተገደሉ

በጋዛ መንግስት ስር የሚተዳደረው ሚዲያ ባወጣው የቅርብ ጊዜ ዘገባ መሰረት ከ24 ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የእስራኤል የቦምብ ጥቃት የተጎጂዎች ቁጥር ከ1,000 በላይ ደርሷል። በጥቃቱ በተረጋገጠ አሃዛዊ መረጃ መሰረት 195 ሰዎች ሲገደሉ፣ 120 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።ቢያንስ 777 ሰዎች በጥቃቱ ቆስለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ማክሰኞ እና እሮብ በጃባሊያ የተፈፀመውን የእስራኤል ጥቃት “አስፈሪ” ሲሉ የገለፁት ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር በበኩላቸው “ያልተመጣጠነ ጥቃት” ወደ “ጦርነት ወንጀሎች” ሊደርስ ይችላል ብለዋል።እስራኤል ጥቃቱ በሀማስ መሪዎች ላይ ያነጣጠረ ነበር ስትል አስተባብላለች።

በሌላ በኩል ከጥቅም 7 ጀምሮ በጋዛ አስራ አንድ ዳቦ ማምረቻ ፋብሪካዎች ተመትተው ወድመዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ አስታውቋል። ከወደሙ ዳቦ ቤቶች ውስጥ ስድስቱ በጋዛ ከተማ፣ ሁለቱ በጃባሊያ፣ ሁለቱ በመካከለኛው አካባቢ እና አንድ በካን ዮኒስ ውስጥ እንደሚገኙ ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።

እስከ እሮብ ድረስ በጋዛ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ዘጠኝ ዳቦ መጋገሪያዎች ብቻ የቀሩ ሲሆን ሰዎች  ዳቦ ለመግዛት ለሰአታት ረጅም ወረፋዎችን እየጠበቁ “ለአየር ድብደባ እየተጋለጡ” ነው ተብሏል። ዳቦ መጋገሪያዎቹ ከድርጅቱ ዱቄት እያገኙ ቢሆንም በነዳጅ እጥረት ምክንያት ሥራቸውን ለመቀጠል እየተቸገሩ መሆናቸውን አስታውቋል።

ዮርዳኖስ በጋዛ ውስጥ ላለው ጦርነት ምላሽ ለመስጠት በማሰብ በእስራኤል የሚገኙትን አምባሳደር በአፋጣኝ እንደሚጠረ አስታውቃለች። እስራኤል “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የሰብአዊ አደጋ” ፈጥራለች ሲል ከሰዋል። “የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ በእስራኤል የዮርዳኖስን አምባሳደር በአስቸኳይ ለመጥራት ወስነዋል” ሲል የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። በጋዛ ውስጥ ንጹሐን ሰዎችን እየገደለ ያለውን የእስራኤል ጦርነት ማውገዛችንን ለማንፀባረቅ ወስነናል ሲል የዮርዳኖስ መንግስት ይፋ አድርጓል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *