መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 23፤2016-የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን ፤ ከፌደራል ተቋማት ህገወጥ የግዢ ፈቃድ ደብዳቤ በብዛት እየደረሰዉ መሆኑን አሳወቀ

የፌዴራል መንግስት ተቋማት ግዢዎቻቸዉን በመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን በኩል እንዲያከናዉኑ ከታወጀ በኋላ በርካታ ተቋማት ህገወጥ የሆነ የግዢ ፈቃድ ጥያቄን ለመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን እያቀረቡ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ መናገራቸውን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

አቶ ሃጂ ፤ “የተቋማት ህገወጥ የሆነ የግዢ ፈቃድ ደብዳቤ ጠረቤዛዬን ሞልቶታል” ያሉ ሲሆን ከህጉ እና አሰራሩ እንዲሁም ተቋማቱ ካስገቡት እቅድ ዉጪ የትኛዉንም ግዢ ተቋማቸዉ እንደማይፈቅድ ተናግረዋል።

ለአብነትም አንዳንድ ተቋማት ለሚገዟቸዉ የተሽከርካሪ ጎማዎች ፣ ሙሉ ልብሶች እና ሌሎች ግብዓቶችን ከለመዷቸዉ አከፋፋዮች ዉጪ የመግዛት ፍላጎት እንደሌላቸዉ ገልጸዋል። ይህም አመታትን በነበሩበት የግዢ ስርዓት ከአምራቾቹ ጋር “ቤተሰባዊ” ግንኙነት እና “የጥቅም ትስስር በመፍጠራቸው ነዉ” ብለዋል።

አሁን የተጀመረዉ የዲጂታል ግዢ ስርዓት ይህንን በማስቀረት ተቋማት በምርታቸዉ ጥራት በፍትሐዊነት የሚወዳደሩበት ነዉ ብለዋል። ማንኛዉም የፌዴራል ተቋምም ካስገባዉ እቅድ ዉጪ ባሰኘዉ ሰዓት ንብረት መግዛት እንደማይችል ጠቁመዋል።

አቶ ሃጂ ፤ አንድ ሀገር ወጪ ቆጣቢ እና ከሙስና የጸዳ የዲጂታል ግዢ ስርዓትን ከጀመረ ከአጠቃላይ ወጪዉ ከ 5 እስከ 25 በመቶኛዉን ማዳን የሚችል መሆኑን ገልጸዉ ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ስርዓት ያተረፈችዉን በሚመለከት በአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ ጥናት እያሰሩ መሆናቸዉንም አክለዋል።

አዲሱ የግዢ ስርዓት ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ መተግበር የጀመረ ሲሆን በዘንድሮዉ አመት ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ 169 የፌዴራል ተቋማት ወደ ዲጂታል የግዢ ስርዓት መግባታቸውን የፌደራል ግዢና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *