መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 26፤2016 – በምን አለሽ ተራ በደረሰ የእሳት አደጋ 41 ሱቆች እና አራት መኖሪያ ቤቶች ወደሙ

በምን አለሽ ተራ በደረሰ የእሳት አደጋ ስድስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።አደጋው ዛሬ ለሊት  7:26 ሰዓት ላይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ምን አለሽ ተራ እየተባለ በሚጠራዉ አካባቢ የደረሰ ሲሆን የእሳት አደጋ ስድስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ሲደርስ በአራት መኖሪያ ቤቶችና በአርባ አንድ የንግድ ሱቆች ወድመዋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት የእሳት አደጋዉ የደረሰባቸዉ  የተለያዩ ቁሳቁሶች ማምረቻና ልዩ ልዩ የንግድ አገልግሎት የሚሰጥባቸዉ ሲሆን የንግድ ሱቆቹም አንድ ሜትር በሁለት ሜትር ገደማ የሚሆኑ እጅግ ጠባብ ሱቆች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር 11 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪና ሶስት አምቡላንሶች ከ69 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር ተሰማርተዋል።የእሳት አደጋዉ የተነሳበት አካባቢ በከተማ ደረጃ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ በጥናት ከተለዩ ቦታዎች መካከል ሲሆን ቤቶቹ የተሰሩበት ግብዓት ፈጣን ተቀጣጣይ የሆኑ ቁሶች የሚመረቱበትና የሚሸጡበትና አካባቢ መሆኑ አቶ ንጋቱ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቲቪ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎችን የሚያስገባ መንገድ አለመኖሩ ለቃጠሎዉ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።ጉዳት የደረሰባቸዉ ሰዎች በእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አምቡላንሶች ህክምና ተደርጎላቸዋል።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር በተደረገዉ ጥረት የጸጥታ ሀይሎች እና የአካባቢዉ ማህበረሰብ እገዛ ያደረጉ ሲሆን እሳቱን ለመቆጣጠር 5 ሰዓት ፈጅቷል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *