መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 26፤2016 – በጅማ ህብረተሰቡን በማደንዘዝ የሌብነት ተግባር ይፈፅሙ የነበሩ ሶስት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

በጅማ ከተማ ወረዳ 2 በቡድን በመደራጀት የማጭበርበር እና የሌብነት ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ ሶስት ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን የከተማው ፖሊስ ገልጿል።

የጅማ ከተማ ወረዳ 2 ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል መርማሪ ሳጅን ኢብራሂም ጀማል ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት አንደኛ ተከሳሽ ፊሊሞን ሀብታሙ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ፍሬዘር ታደሰ እና ሶስተኛ ተከሳሽ በይን ሀይሌ የተባሉ ግለሰቦች ወንጀሉን እንደፈፀሙት ተናግረዋል።

እንዲሁም ከባጃጅ አሽከርካሪ ጋር ቅንጅት በመፍጠር በንግድ ተቋማት ውስጥ በመግባት የተለያዩ ሸቀጦችን እንደሚገዙ በማስመሰል የማጭበርበር ተግባር በመፈፀም ከነጋዴዎች ላይ ገንዘብ በማጭበርበር እንደሚወስዱ በማስረጃ መረጋገጡንም ገልፀዋል።

ሶስቱ ግለሰቦች ጥቅምት 29 ቀን 2015ዓ.ም ከአንድ ህንፃ መሳሪያ መደብር በመግባት የግድግዳ ቀለም የሚገዙ በማስመሰል የንግድ መደብሩን ባለቤት ምንነቱ ባልታወቀ ነገር በማደንዘዝ በንግድ መደብር ውስጥ ከሽያጭ የተቀመጠ 28ሺ ብር ሰርቀው መሰወራቸውን ተናግረዋል።

ፖሊስ በተደጋጋሚ በጅማ ከተማ ተመሳሳይ የማጭበርበር እና የስርቆት ወንጀል ሰውን በማደንዘዝ እየተፈፀመ መሆኑን ከደረሱት ሪፖርቶች በማረጋገጡ ባደረገው ክትትል ሶስቱ ግለሰቦች በተመሳሳይ ድርጊት ሲሰማሩ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።

ፖሊስ ና የግለሰቦቹን የምርመራ መዝገብ አጣርቶ  ለዓቃቢ ህግ የላከ ሲሆን ዓቃቢ ህግ ክስ በመመስረት ለበደሌ ከተማ ፍርድ ቤት ልኳል።

ፍርድ ቤቱም አንደኛ ተከሳሽ ፊሊሞን ሀብታሙ በ4 ዓመት  እስራት ሁለተኛ ፣ ተከሳሽ ፍሬዘር ታደሰ በ3ዓመት ከ6ወር እስራት እና 3ኛ ተከሳሽ በየነ ሀይሌ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ረዳት ኢንስፔክተር ኢብራሂም ጀማል ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በምህርት ታደሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *