???? ፖሊስ ለምርመራ አስክሬን ከመቃብር እንዲወጣ አድርጓል
በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ግራዋ ወረዳ ቡሮ ቀበሌ ለወላጆቹ የመጨረሻ ልጅ የሆነው ኢብራሂም ሀሰን ቃል የተገባለትን ውርስ በቶሎ ለማግኘት ባለመቻሉ ወላጅ አባቱን ገድሎ ገደል ውስጥ መጣሉን የግራዋ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ዋንጋሪ ጄቤሳ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
አባት አቶ ሀሰን አብደላ በአጠቃላይ ከኢብራሂም ጋር አምስት ልጆች ያሏቸው ቢሆንም ሌሎቹ ልጆች አግብተው ከቤት መውጣታቸውን ተከትሎ ለመጨረሻ ልጃቸው ኢብራሂም በሚገባ ከጦርከኝ ሙሉ ሀብቴን አወርስሃለው በማለት ቃል ገብተዉለት እንደነበረ ተነግሯል፡፡
ይሁን እና አባት እድሜ ቢጫናቸውም ህይወታቸው አለማለፉ እና ልጅም ቃል የተገባለት ሃብት በጣም በመጓተቱ አባቱን ገድሎ ጥልቀት ባለው ገደል ውስጥ መወርወሩ ተረጋግጧል፡፡ ልጁም አባቱን ከገደለ በኋላ ለፖሊስ እንዲሁም ለቤተሰብ አባቱ መጥፋቱን እና ወደ ቤት አለመምጣታቸውን ያመለክታል፡፡
ፖሊስ እና የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረገው ፍለጋ ህይወታቸዉ አልፎ ገደል ውስጥ አስከሬናቸው ይገኛል ፡፡ በማህበረሰቡ ትብብር ስርዓተ ቀብራቸዉ ከተፈጸመ በኋላ ግድያ ተፈጽሞባቸዉ ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ የአስከሬን ምርመራ እንዲደረግ በተጠየቀው መሰረት ምርመራው እንዲደረግ ይወሰናል፡፡ከአንድ ወር ከሁለት ሳምንት በኋላ ልጅ የአባቱ ደም እንቅልፍ ያሳጣዋል በዛም መጠጥ ሲጠጣ ቆይቶ ቀበሌ ላይ በአመራርነት ለሚሰራ ወዳጁ የፈጸመውን ድርጊት ይነግረዋል ።
በአካባቢው በዓል መሰረት የአውጫጭኝ የተሰኘ ስርዓት በመጠቀም ወላጅ አባቱን ገድሎ ገደል መክተቱን ያምናል፡፡ ፖሊስ አስከሬን ምርመራም መገደላቸውን በማረጋገጡ ተከሳሹን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የግራዋ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ዋንጋሪ ጄቤሳ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
በኤደን ሽመልስ