መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 28፤2016 –በአሽከርካሪው ላይ ድብደባ በመፈፀም የመኪና ስርቆት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ!!

አገልግሎት ፈላጊ በመምሰል እና አሽከርካሪዎችን በማስፈራራት ሁለት ተሽከርካሪዎችን የሰረቁ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።

ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ሁለት ግለሰቦች ከሌሊቱ 6 ሰዓት ገደማ  የሰሌዳ ቁጥር ኮድ3- B15712 አ.አ አሽከርካሪን ከገርጂ ወደ መገናኛ እንዲያደርሳቸው ከተስማሙ በኋላ አሽከርካሪውን  በመደብደብ ተሽከርካሪውን ቀምተው ያመልጣሉ፡፡

የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት የደረሰው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ  ባደረገው ክትትል ወንጀል ፈፃሚዎቹን ከእነ ተሽከርካሪው በቁጥጥር  ስር አውሏል፡፡

እነዚሁ ወንጀል ፈፃሚዎች  ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ/ም በተመሳሳይ ዘዴ አሽከርካሪን በማስፈራራትና በመደብደብ  የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- A75796 አ.አ  ተሽከርካሪን ይዘው ከተሰወሩ በኋላ  የሰረቁትን መኪና በ200ሺ ብር እንደሸጡ እና ገዢውም አሳልፎ ለሌላ ግለሰብ እንደሸጠው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ባደረገው ምርመራ  አረጋግጧል፡፡

ፖሊስ የተሰረቁትን ሁለት ተሽከርካሪዎች ያስመለሰ ሲሆን በአጠቃላይ በዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ አላቸው የተባሉ አምስት ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ የተጣራባቸው ሲሆን በግለሰቦቹ ላይ ክስ እንዲመሰረት መዝገቡን  ለአቃቤ ህግ መላኩን አስታውቋል፡፡ 

የተሰረቁ ንብረቶችን የሚገዙ ህገ-ወጦች ለመሰል ወንጀል መበራከት ምክንያት በመሆናቸው ፖሊስ የተሰረቁ እቃዎችን የሚገዙ ህገ-ወጦችን ለመቆጣጠር እያደረገ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *