
የደቡብ አፍሪካ የትራንስፖርት ሚንስትር የተሽከርካሪዋ ጎማ መፈንዳቱን ተከትሎ በፍጥነት መንገድ ወይም ሀይዌይ ላይ ጎማ ለመቀየር ከቆመች በኋላ በጠመንጃ አፈሙዝ እንዴት እንደተዘረፈች ተናግራለች። ሚኒስትሯ ሲንዲሲዌ ቺኩንጋ ለፓርላማ ኮሚቴ እንደተናገረችው የደረሰባት ዝርፊያ ጭንብል ያደረጉ አጥቂዎች መካከል አንዱ ሽጉጡን ጭንቅላቷ ላይ መደቀኑን ገልፃለች።
ሌቦቹ ላፕቶፖች፣ስልክ እና የጠባቂዎቿን መሳሪያ እንደዘረፉ ተናግራለች። ደቡብ አፍሪካ በመኪና ጠለፋ፣ አፈና ፣ ድብደባ እና ዝርፊያን ጨምሮ ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ይፈፀምባታል። ነገር ግን በመንግስት ሚንስትር ደረጃ የታጠቁ ጠባቂዎችን ይዛ በተሽከርካሪው ውስጥ መዘረፉ ያልተለመደ አድርጎታል።ሚኒስትሯ ቺኩንጋ ለፓርላማ አባላት እንደተናገረችው ከጆሃንስበርግ በስተደቡብ ባለው ዋና መንገድ ላይ ሲንጓዝበት የነበረው መኪና ጎማ መፈንዳቱን ተከትሎ ለመተካት እንደወረዱ ዘራፊዎቹ ቀርበው ጠባቂዎቼን መሬት ላይ አስገድደው አስተኝተዋል ስትል ተናግራለች።
ገንዘብ ቢጠይቁም ምንም አይነት ገንዘብ እንደሌለኝ አስረድቻቸዋለሁ። ከዚያም በተሽከርካሪ ውስጥ ያገኙትን ፈትሸው ወስድዋል። ሚኒስትሯ ፈርቼ ስለነበረ መጸለይ ስጀምር ዝም እንድል አስገደዱኝ ብለዋል። ቺኩንጋ ስለተፈጠረው ነገር ገለጻዋን ስትጨርስ “ደህና ነን፣ ጤነኞች ነን፣ በህይወት አለን:: ይህ አሰቃቂ ገጠመኝ ነበር ግን እግዚአብሔር ማረን” ስትል ለፓርላማ አባላት ተናግራለች።
ፖሊስ ዘረፋው መፈፀሙን አረጋግጧል። ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ክስተት ተከትሎ ወንጀለኞችን የማደን ስራ መጀመሩን የፖሊስ ቃል አቀባይ ብሪጅ አትሌንዳ ማቲን ተናግረዋል።የትራንስፖርት ሚኒስቴር ወንጀለኞች የሚጠቀሙበትን የተለመደ ዘዴ እንዳለ በመጥቀስ የመኪና ጎማዎች እንዲፈነዱ በመንገድ ላይ ስል ቁሳቁሶችን በማስቀመጥ አሽከርካሪዎች መኪናቸው እንዲቆም በማድረግ ዝርፊያ ይፈፅማሉ።
የሚኒስትሯ ሁለቱ ጠባቂዎች በአቋም ደረጃ ብቁ እስከሚሆኑ ድረስ ከስራቸው ተነስተዋል።የቪአይፒ ጥበቃ ፕሮቶኮልን በተመለከተ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል። በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ዓመታዊ ጥናት ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የንብረት ወንጀል ሰለባ መሆናቸውን ያሳያል፣ ይህም ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ 3 በመቶ ያህል ነው።
በስምኦን ደረጄ