አመታትን ያለ አገልግሎት በየመንግስት መስሪያቤቶች የቆሙ እና የኋላ ታሪካቸዉ የጠፋ ተሽከርካሪዎችን ለመሸጥ መላ እያፈላለገ መሆኑን የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን አስታዉቋል።
የግዢና ንብረት ባለስልጣን መስሪያቤቱ ፤ የቆዩ እና የተከማቹ ንብረቶችን ከማስወገድ አኳያ የቆሙ ተሽከርካሪዎች የኋላ ታሪክ መጥፋት ፈተና እንደሆነበት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ መናገራቸውን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።
ባለስልጣኑ አደረኩት ባለዉ ዉስን ማጣራት በጣት የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ብቻ የኋላ ታሪካቸው መገኘቱን አቶ ሀጂ አንስተዋል። ይህም ንብረቶቹን ለሶስተኛ አካል ለማስተላለፍ እንቅፋት የሚፈጥር ሲሆን በመኪናዎቹ ከዚህ ቀደም ወንጀል ተሰርቶ መሆኑን እንኳን ማጣራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ታድያ እነዚህ የኋላ ታሪካቸው ጠፍቷል የተባሉ ተሽከርካሪዎችን ለመሸጥ ባለስልጣኑ መላ እየፈለገ መሆኑንም አቶ ሀጂ አንስተዋል። ለአብነትም በተሽከርካሪዎቹ የተፈጸመ ወንጀል እንኳን ቢኖር የገንዘብ ሚኒስቴር አልያም ሌላ የሚኒስቴር መስሪያቤት ዋስትና ሰጥቶ እንዲሸጡ ሲሆን ሌላኛዉ በቁርጥራጭ ብረታብረት አማካኝነት ማስወገድ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በመንግስት አንዳንድ መስሪያቤቶች በቀላል ጥገና ጭምር አገልግሎት መስጠት እየቻሉ አመታትን የቆሙ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ የተነገረ ሲሆን በላያቸዉ ላይ ሌላ የተሽከርካሪ ግዢ ይፈጸም እንደነበርም ተሰምቷል።
በበረከት ሞገስ