በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ህፃናት መካከል 75 በመቶ ወይንም 44 ሚሊየን ህፃናት በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ እና መሰረታዊ ፍላጎታቸው እንዳልተሟላላቸው አፍሪካን ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም ገልጿል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሁኔታ ህፃናት ለድህነት እና ለረሃብ እንደሚጋለጡ የአፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም የፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ የኋላእሸት መኮንን ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በአፍሪካ የልጆችን ድህነት እና ርሀብ ከማስቀረት አንፃር ብዙ ስራ እንደሚቀር እና የአብዛኞቹ ህፃናት መሰረታዊ ፍላጎታቸው አልተሟሉላቸውም ብለዋል።በዚህ ችግር ተጋላጭ የሚሆኑት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ እና በሰላም እጦት ምክንያት ከቦታ ቦታ የሚፈናቀሉ ህፃናት እንደሆኑም ገልፀዋል።
ይህ የህፃናት ረሀብ በአፍሪካ 54 በመቶ ወይንም ከ350 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ህፃናት እንዳሉም እና ከነዚህም መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙም ተናግረዋል።እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ 110 ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት በድህነት የመውደቅ አደጋ ላይ መሆናቸውን እና ይህ ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ ነው ብለዋል።
የህፃናት ረሀብ ወይንም ህፃናት ተርበዋል የሚለውን መረጃ መለመድ እንደሌለበት እና ሀገራት ከፍተኛ ስጋት ላይ እንዳሉ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል ።አክለውም ህፃናቱ በሚያጋጥማቸው የከፋ ድህነት ወይንም ረሀብ ምክንያት የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት እና የመቀንጨር አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ጨምረው ተናግረዋል።
በምህረት ታደሰ