መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 8፤2016 – በአዲስ አበባ ከተማ በዛሬው እለት የጣለው ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ 18 መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ደረሰ

ዛሬ ቅዳሜ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሰፈራ እየተባለ በሚጠራዉ አካባቢ ከሰዓት በኋላ የጣለዉን ዝናብ ተከትሎ በተፈጠረ የጎርፍ  አደጋ 18 መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት በጎርፍ አደጋዉ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸዉ ነዋሪዎች በጊዚያዊነት በአቅራቢያዉ ባለ ትምህርት ቤት እንዲጠለሉ ተደርጓል።

ለጎርፍ አደጋ ምክንያት የሆነዉ በአካባቢዉ ያለዉ ወንዝ ከፍተኛ መጠን ባለዉ የአፈር ተረፈ ምርት በመዘጋቱና ጎርፍ ወንዙን ተከትሎ እንዳይሄድ በማድረጉ ነዉ።

ይህንን ከፍተኛ መጠን ያለዉ አፈር ለማንሳት ማምሻዉን ድረስ ጥረት ቢደረግም አፈሩን ሙሉ በሙሉ ማንሳት አለመቻሉን አቶ ንጋቱ ጨምረው ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ገልፀዋል።

ሌሊቱን ተመሳሳይ ዝናብ ቢዘንብ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በትምህርት ቤት እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን በነገዉ ዕለት ተጨማሪ ማሽነሪዎችን በማሰማራት ችግሩ ሙሉ በሙሉ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል።

የኮንስትራሽን ስራዎችና መሰል ተረፈ ምሮቶች አወጋገድ ላይ አስፈላጊዉ ጥንቃቄ አለማድረግ እንዲህ ዓይነት ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ አካላት ተገቢዉን ቁጥጥር እንዲያደርጉ ኮሚሽን መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *