
???? ባንኩ የምስረታውን 25ኛ ዓመት ማክበር ጀምሯል
ሕብረት ባንክ የ25ተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓሉን በይፋ በዛሬው ዕለት ያበሰረ ሲሆን በየዓመቱ ከ25 እስከ 30 በመቶ እድገት እያስመዘገበ መምጣቱን ባንኩ አስታውቋል ።
ባንክ ባለፉት 25 ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደዘለቀ የተገለፀ ሲሆን ከ15 ዓመታት በፊት ሞባይል ባንኪንግን ኤስኤምኤስ ባንኪንግ በሚል በመጀመር ቀዳሚ ባንክ እንደሆነ የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አ/ቶ መላኩ ከበደ መናገራቸውን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል ።
በተጨማሪ ባንኩ የኮር ባንኪንግ ሲስተም ከውጭ ሀገር ዜጎች ውጭ በራሱ ሰራተኞች መተግበሪያ በማበልፀግ በኢትዮጵያ ብቸኛው ባንክ መሆኑንን አ/ቶ መላኩ ተናግረዋል ።
ሕብረት ባንክ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ካፒታሉ 9 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ፣ 60 ቢሊዮን ብር ብድር ፣ 64 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ያለው ሲሆን የሃብት መጠኑ 83 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተነግሯል ። የ25ተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓሉን ዓመቱን በሙሉ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚያከብርም ተጠቁሟል ።
በአበረ ስሜነህ