
???? አስከሬኖቹን ከተሽከርካሪዎቹ ስር ለማውጣት ከአንድ ሰዓት በላይ ፈጅቷል
በአዲስ አበባ ከተማ ትላንት ህዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 2:19 ሰዓት ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አዲሱ ቦሌ ቡልቡላ መንገድ ወይም ጃፋር መስኪድ ፊት ለፊት በደረሰ የትራፊክ አደጋ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌባቪዥን እንደተናገሩት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-ኢት 0364259 የሆነ ሲኖ ትራክ ተሽከርካሪ ባደረሰዉ የትራፊክ አደጋ እድሜያቸዉ ሰላሳ ዓመት የተገመቱ ሁለት ወንዶች ህይወታቸዉ አልፏል።
ማቾቹ በአካባቢው ምሽት ላይ ተሽከርካሪዎች ጎዳና ላይ የሚጠብቁ ሲሆኑ በቆርቆሮ የተሰራች ተቀሳቃሽ ማደሪያቸውን ተደግፈው እያወሩ ሳለ ተሽከርካሪው መንገድ ስቶ ከቆመ የአፈር መዳመጫ ተሽከርካሪ ጋር እንዳጣበቃቸው ለማወቅ ችለናል።
የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የሟቾቹን አስከሬን ከተሽከርካሪዉ ስር ለማውጣት ከአንድ ሰዓት በላይ እንደፈጀባቸው አቶ ንጋቱ የነገሩን ሲሆን አስከሬናቸውን አዉጥተዉ ለፖሊስ አስረክበዋል።
የአደጋዉን መንስኤ ዝርዝር ጉዳይ ፖሊስ እያጣራ ነዉ።
በትግስት ላቀው