
በመላው ብራዚል ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል መኖሩ የተመላከተ ሲሆን ክብረ ወሰን በተባለ ደረጃ 44.8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን ተመዝግቧል።
የሙቀት ክብረወስኑ የተመዘገበው እሁድ እለት በብራዚል ደቡብ ምስራቅ በምትገኘው ሚናስ ገራይስ በምትገኘው አራኩዋይ ከተማ ነው። ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ይህ የአየር ሁኔታ ሊመዘገብ የቻለው በኤልኒኖ ክስተት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ነው ተብሏል። ትንበያዎች እንደሚያሳዩት የሙቀት መጠኑ በዚህ ሳምንት ሊቀንስ እንደሚችል ተጠቁሟል።
እንደ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ተቋም ዘገባ ከሆነ፣ የሙቀት መጠኑ ወደ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሶስት የብራዚል ግዛቶች ዋና ከተሞች ላይ ሊመዘገብ እንደሚችል አስታውቋል።የመንግስት ኤጀንሲው እንዳስታወቀው ከዚህ ቀደመ 2005 ከተመዘገበው 44.8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከደረሰው ሙቀት የአራኩዋይ ከተማ 44.7 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሷል ሲል ጠቁሟል። ሙቀቱ በደቡብ ንፍቀ ክበብ ከመጀመሩ አንድ ወር በፊት በመላ አገሪቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር።
ሰዎች እራሳቸውን እና ቤታቸእን ለማቀዝቀዝ በሚሞክሩበት ወቅት የብራዚል የኃይል ፍጆታ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተነግሯል።ከፍተኛ ሙቀቱ እውቋ ድምፃዊት ቴይለር ስዊፍት በሪዮ ዲጄኔሮ ከተማ የነበራትን ኮንሰርት እንድትሰርዝ ያስገደዳት ሲሆን ከትዕይንቱ በፊት አንዲት አድናቂዋ ሙቀቱ ባስከተለው የጤና እክል ህይወቷ ማለፉ ኮንሰርቷን እንድትሰርዝ አድርጓታል።
እንደ ኮንሰሩት አዘጋጆቹ ገለጻ ከሆነ የ23 ዓመቷ አና ክላራ ቤኔቪዴስ ማቻዶ የሙዚቃ ድግሱ በተዘጋጀበት ስታዲየም እርዳታ ጠይቃ የነበረ ሲሆን ወደ ሆስፒታል በተወሰደች ከአንድ ሰአት በኋላ ህይወቷ አልፏል። ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በሀገሪቱ ያለው አማካይ የሙቀት መጠን ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ውስጥ ከአማካይ በላይ ነበር። በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በአለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ እና ኃይለኛ ሙቀት እየተመዘገበ ይገኛል።
እንደ ሳይንቲስቶች ገለጻ፣ የሙቀት ሞገዶች በበርካታ የአለም አካባቢች እየጠነከሩ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ምድር በአሁኑ ጊዜ በኤልኒኖ የአየር ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፣ በዚህ ጊዜ የአለም ሙቀት በአብዛኛው ይጨምራል።
በስምኦን ደረጄ