መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 11፤2016 – የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ ከብሩኪናፋሶ ጋር ወሳኝ ጨዋታውን ያደርጋል

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ወሳኝ ጨዋታውን ከብሩኪና ፋሶ ብሔራዊ ቡድን ጋር በሞሮኮ ኤል አብዲ ስታዲየም ዛሬ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያና ብሩኪናፋሶ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ቀደም ሲል ምሽት አራት ሲዓት ላይ ሊደረግ ፕሮግራም ወጥቶለት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረበው ቅሬታና የሠዓት ለውጥ ጥያቄ መሰረት የጨዋታው ሰዓት ከምሽት አራት ሰአት ወደ ቀኑ 10 ሰዓት እንዲቀየር ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከብሩኪና ፋሶ አቻው ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ምድቡን በተሻለ ደረጃ ላይ ለማጠናቀቅ ከሚያስችሉ ቁልፍና ወሳኝ ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ከዚህ ምድብ ብዙዎች ቅድመ ግምቱን ለግብፅና ብሩኪና ፋሶ ሰጥተዋል፡፡ እናም ይህን ቅድመ ግምት ፉርሽ ለማድረግ ኢትዮጵያ በዛሬው ጨዋታ የምታስመዘግበው ውጤት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ምድብ እስከ ውድድሩ ፍፃሜ በፉክክር ውስጥ ለመቆየት አሊያም ታሪክ ለመስራት ብሩኪና ፋሶን ማሸነፍ አሊያም ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ያስፈልጋታል፡፡ አሰልጣኝ ገ/መድህን ሃይሌና ልጆቻቸውም ይሄን ለማድረግ ጠንክረውና በርትተው እየሰሩ እንደሚገኙ ከስፍራው የሚደርሱን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ለዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ከመስመር አጥቂው በረከት ደስታ በስተቀር ሌሎች ሁሉም ተጨዋቾች ለጨዋታው በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡

አሰልጣኝ ገ/መድህን ሃይሌ ለዛሬው ጨዋታ የሴራሊዮኑን ቋሚ አሰላለፍና የአጨዋወት መንገድ ይዘው ሊቀርቡ እንዳሰቡም ሰምተናል፡፡  የብሩኪና ፋሶ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከጊኒ ቢሳኦ ጋር አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት መለያየቱና ግብፅ ምድቡን ገና ከወዲሁ በ6 ነጥብ መምራቷ ለዛሬው ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ እንዳደረገውም ታውቋል፡፡ ቡድኑ ለዛሬው ጨዋታ ወሳኝ ተጨዋቾቹን ከያሉበት ማሰባሰቡን ብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

የብሩኪና ፈሶ ብሔራዊ ቡድን የተዋቀረው በአብዛኛው በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በሚጫወቱ ተጨዋቾች ሲሆን ከሀገሩ ውስጥ ክለቦች የተመረጡት አንድ እጅ የማይሞሉ እንደማይሞሉም ተሰምቷል፡፡ ስለዚህ የዛሬው ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱም ዘንድ ከፍተኛ ትኩረትና ግምት የተሰጠው ጨዋታ በመሆኑ ጥሩ ፉክክር ይታይበታል የሚል ቅድመ ግምትን አግኝቷል፡፡ ዛሬ ቀን 10 ሰዓት ላይ የሚጀመረውን የሁለቱ ሀገራትን ጨዋታ ጋምቢያዊ ዋና ዳኛ የሚመራው ይሆናል፡፡   

በጋዜጠኛ መላኩ ወ/ሰንበት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *