
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ ሞልቶ በመፍሰሱ በዳሰነች ወረዳ ከሚገኙ 40 ቀበሊያት ዉስጥ 34 ቀበሌዎችን ማጥለቅለቁ ተነግሯል ።
ወንዙ 79,828 የቤተሰብ አባላትን ያፈናቀለ ሲሆን ቀደም ሲል ከ62 ሺህ በላይ ሰዎችን አፈናቅሎ ቆይቶ በቅርቡ ደግሞ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉ ተገልጿል ።
በተፈጠረው የውሃ መጥለቅለቅ በተቋማት ላይ ከፍተኛ አደጋ ያስከተለ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 2 ጤና ጣቢያ፣ 17 ትምህርት ቤቶች እና ሌሎችም ተቋማት ሙሉ በሙሉ በውሃ ተሸፍኗል። በተጨማሪም 123 ሺህ ሄክታር የእንስሳት የግጦሽ መሬት ሙሉ በሙሉ በውሃ መሸፈኑ ተጠቁሟል ።
በአሁኑ ወቅት በወረዳዉ የሚገኙ 21 ደሴቶች ዉስጥ የሚኖሩ የቤተሰብ አባላትና ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንስሳቶች በውሃ ሙላት ሲከበቡ ከነዚህም ዉስጥ ከ89 ሺህ በላይ ከብቶች ብቻ ማዉጣት መቻሉን የዳሰነች ወረዳ አስተዳዳሪ አ/ቶ ፍቅረማሪያም አይመላ ከብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል ።
ወረዳው ከፌዴራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጋር ወይይት ማድረጉ የተገለፀ ሲሆን አንድ ጀልባ ወደ ወረዳው መግባቱ ተገልጿል ። በአደጋው ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍ ያደረጉ ቢሆንም ከጉዳቱ አንፃር ተጨማሪ ድጋፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመተባበርና በመቀናጀት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል ።
በአበረ ስሜነህ