መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 11፤2016 – የ40 ዓመት የትዳር አጋሯን “ከሌላ ሴት ልጅ ለመውለድ” ፈልጓል በሚል በመጥረቢያ የገደለችው ግለሰብ በእስራት ተቀጣች

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ወረዳ  01 ቀበሌ የትዳር አጋሯን ከሌላ ሴት ልጅ ለመውለድ ፈልጓል በማለት በመጥረቢያ ቆራርጣ የገደለችው ግለሰብ  በእስራት መቀጣቷን የኦሮሚያ የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።አቶ ዳዲ አዱኛ እና ወይዘሮ ጸሃይ በትዳር ለ40 ዓመታት የኖሩ ሲሆን ስምንት ልጆችን ወልደው ለመሳም በቅተዋል።ጥንዶች የሚተዳደሩበትን የእህል ወፍጮ ፣የእህል መሸጫ በረንዳ  በንብረትነት ማፍራት ችለዋል። 

ባል የ72 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ እንዲሁም ሚስታቸው የ57 ዓመት አዛውንት መሆናቸውን
የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር መላኩ ቶላ  በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል። ባል ልጅ እፈልጋለሁኝ  በማለት ለዘመድ እና ጎረቤቶቻቸው በተደጋጋሚ በሚያወሩት ወሬ ሚስታቸው ደስተኛ  አለመሆናቸው እና በመካከላቸው በተፈጠረ ግጭት ልጆቻቸው ሲያስታርቋቸው መቆየታቸው ተነግሯል።

ወይዘሮ ጸሃይ የካቲት 6 ቀን 2015 ምሽት ላይ ጎረቤት ቡና እየጠጡ  ባሉበት ሰዓት የሚሰሙት የሀሜት ወሬ የቅናት ስሜት ይጭርባቸዋል። ሚስትም በቅናት ለባለቤታቸው ጎረቤት ሁሉ የሚያወራው እውነት መሆኑን ጠይቀው ባልም በመጠጥ ግፊት አዎ ልጅ እፈልጋለሁ ብለው መመለሳቸው ተጠቁሟል። በዚህም በቅናት መተኛት ያቃታት ሚስት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በመነሳት በእንጨት መፍለጫ ባለቤቷን  አንገት በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጓ ተገልጿል።

ተከሳሿ የፈሰሰውን ደም ካጸዳች በኋላ  አስከሬኑን ለመጣል በሞከረችበት ሰዓት  በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውላለች ። ፖሊስ ወንጀሉን አጣርቶ እና የአስከሬን ምርመራ ካደረገ በኋላ መዝገቡን በመረጃ እና በማስረጃ በማጠናቀር ለፍርድ ያቀርባል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ወይዘሮ ጸሃይን ጥፋተኛ በማለት በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ የወሰነባቸው መሆኑን  ረዳት ኢንስፔክተር መላኩ ቶላ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *