መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 11፤2016 – ፕሬዝዳንት ሩቶ ለ200 ሺ ኬንያዊያን በጀርመን የስራ እድል እንዲፈጠር እየሞከሩ መሆናቸውን ተናገሩ

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሀገራቸው እየተባባሰ ያለውን የስራ አጥነት ቀውስ ለመቅረፍ ኬንያውያን በጀርመን ውስጥ ስራ የሚያገኙበትን እድል ለማስገኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል። ለቡድን 20 ስብሰባ ወደ አውሮፓ ከመሄዳቸው አስቀድመው ዊሊያም ሩቶ ይህንኑ ንግግር አድርገዋል።

ከደርዘን በላይ የአፍሪካ መሪዎች የሰራተኛ የውጪ ሀገር የስራ ስምምነቶችን እና በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ኢንቨስትመንት መጨመርን በማለም የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለመፈለግ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ይገኛሉ። የጀርመን ቻንስለር ከአራት ወራት በፊት በኬንያ ነበሩ። ሩቶ ወደ ጀርመን እየተጓዝኩ ነው ምክንያቱ ደግሞ 200,000 ስራዎችን እንደምናገኝ ቃል ተገብቶልን ነበር ሲሉ አክለዋል።

እነዚያን እድሎች መከታተል አለብኝ ሲሉ ገልፀዋል። ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ በቅርቡ በአፍሪካ ያደረጉት ጉብኝቶች ኬንያን እና ናይጄሪያን ያካተተ ሲሆን በአህጉሪቱ በተለይም ወሳኝ በሆኑ ማዕድናት እና አረንጓዴ ኢነርጂ ዘርፎች ላይ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ፍላጎት አሳይተዋል ። ይህ ጉባኤ በቡድን 20 ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ እና በቡድን 20 ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው።

13 የአፍሪካ ሀገራት የፕሮግራሙ አካል ናቸው። እነዚህም ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ አይቮሪ ኮስት፣ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ቶጎ እና ቱኒዚያ ናቸው። በዝግጅቱ የኢትዮጵያ ፣ ኬንያ እና ናይጄሪያን ጨምሮ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በእንግድነት ተሳትፈዋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *