መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 – በኦሮሚያ ክልል በገና ዋዜማ እና በእለቱ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ9 ሰዎች ህይወት አልፏል

በኦሮሚያ ክልል በ2016 ዓ.ም  ቅዳሜ እና እሁድ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ9 ሰዎች ህይወት አልፏል። በአጠቃላይ በሁለቱ ቀናት ስምንት የትራፊክ አደጋ የደረሰ ሲሆን በእነዚህም  የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሌሎች አስራ አንድ  ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ  የአካል ጉዳት መድረሱን በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር ክፍል ባለሙያ የሆኑት ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

ከደረሱት  አደጋዎች መካከል ሁለቱ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ ሲሆን  አንዱ ደግሞ  በንብረት ላይ ጉዳት ያስከተለ አደጋ  መሆናቸው ተጠቁሟል። ባለፉት ሁለት የበዓል ቀናት ማለትም ቅዳሜ እና እሁድ ውስጥ በደረሱ የትራፊክ  አደጋዎች በንብረት ላይ   ከፍተኛ  ውድመት መድረሱ ተጠቁሟል ።

አደጋዎቹ  በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች የተከሰቱ መሆናቸው ተጠቁሟል። የአደጋዎቹ  መንስኤዎቹ ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት፣ ያለመንጃ ፍቃድ ማሽከርከር እና በፍጥነት ማሽከርከር መሆኑን ኢንስፔክተር መሰለ አበራ  ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በበዓል ቀናት  ሆነ በማንኛውም የስራ ቀናት ሁሉም አሽከርካሪዎች  ራሳቸውን ጠብቀው ህጉን አክብረው ማሽከርከር ራሳቸውንም  ማህበረሰቡን ከአደጋ መጠበቅ  እንደሚገባቸው  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *