መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 – የደቡብ ኮሪያ መንግስት የውሻ ስጋ ንግድን የሚከለክል ህግ በዛሬዉ እለት ይፋ አደረገ

ደቡብ ኮሪያ አዲስ ህግ ያወጣች ሲሆን በፈረንጆቹ 2027 ውሾችን ለእርድና ስጋቸውን መሸጥን ለማስቆም ያለመ ነው ተብሏል።

ህጉ ለዘመናት የቆየውን የውሻ ሥጋ የመብላት ልምድን ለማስወገድ ያስችላል፡፡የውሻ ሥጋ ላለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት በተመጋቢዎች ዘንድ ተቀባይነቱ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን የደቡብ ኮርያ ወጣቶች እንደ ወላጆቻቸዉ ዘመን የዉሻ ስጋን ለመመገብ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡በህጉ መሰረት ውሾችን ማራባት ወይም ለምግብ ማረድ እንዲሁም የውሻ ስጋን ማከፋፈል ወይም አልያም የተከለከለ ነው ። ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰዉ ወደ ማረሚያ ቤት ሊወርድ እንደሚችል ህጉ ያስገድዳል፡፡

የውሻ ሥጋን የሚያመርቱ ወይም የውሻ ሥጋ የሚሸጡ ቢበዛ ለሁለት ዓመት ሊቆዩ የሚችል እስር ይጠብቃቸዋል። ይሁን እንጂ የውሻ ሥጋን መመገብ በራሱ ሕገ-ወጥ እንዳልሆነ መመሪያዉ ያሳያል፡፡አዲሱ ህግ ከሶስት አመት በኋላ ስራ ላይ የሚውል ሲሆን ለዉሻ አርቢዎች እና የዉሻ ስጋ አቅራቢ ሬስቶራንት ባለቤቶች አማራጭ የስራ እና የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ጊዜ ይሰጣል። ንግዶቻቸውን ለማስቀረት የስራ እቅድ ለአካባቢያቸው ባለስልጣናት ማቅረብ አለባቸው።

መንግሥት የውሻ ሥጋ አምራቾን፣ ሥጋ ቤቶችንና ሬስቶራንት ባለቤቶችን ከዚህ ስራ እንዲወጡ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ ቃል ገብቷል፡፡ የንግድ ሥራቸው እንዲዘጋ የሚገደዱ ቢሆንም፣ ምን ዓይነት የካሳ ክፍያ እንደሚፈጸም ግን ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የተባለ ነገር የለም፡፡ በመንግስት አሀዛዊ መረጃ መሰረት ደቡብ ኮሪያ እስከ 2023  ዓመት ድረስ ወደ 1,600 የውሻ ስጋ ምግብ ቤቶች እና 1,150 የውሻ አርቢዎች እንዳሏት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የደቡብ ኮሪያ አርሶአደሮች መንግስት የውሻ ስጋ ለምግብነት እንዳይቀር ለማገድ የሚያስችል ረቂቅ ህግ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ከፖሊስ ጋር ባለፈዉ ወር መጋጨታቸዉ ይታወሳል።ውሻን ለምግብነት ሲያረቡ እና ሲያሳድጉ የነበሩ 200 ገደማ የደቡብ ኮሪያ አርሶአደሮች መንግስት የውሻ ስጋ እንዳይበላ ለማድረግ ያወጣውን እቅድ እንዲሰርዝ በፕሬዝደንቱ ጽ/ቤት አቅራቢያ ዉሾቻቸዉን ለመልቀቅ አቅደዉ ነበር፡፡

“ቦሺንታንግ” ተብሎ የሚጠራው የውሻ ስጋ  በአንዳንድ የደቡብ ኮሪያውያን አዛውንቶች ዘንድ እንደ ጣፋጭ ምግብ የሚቆጠር ቢሆንም ስጋው በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ አይደለም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *