መደበኛ ያልሆነ

ጥር 1፤2016 – በኢኳዶር ታጣቂዎች በቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት ላይ ወረራ ከፈጸሙ በኃላ ወንጀለኞችን ለመደምሰስ ጦርነት ከፈተች

የኢኳዶሩ ፕሬዝዳንት ለቀናት የዘለቀው ሁከት በቴሌቭዥን ስቱዲዮ ላይ በተፈጸመ ጥቃት መጠናከሩን ተከትሎ የወንጀለኛ ቡድኖች “ገለልተኛ እንዲሆኑ” አዘዋል።ጭንብል የለበሱ ታጣቂዎች በቀጥታ ስርጭት ወቅት የህዝብ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነዉን ቲሲ የቀጥታ ስቱዲዮን ሰብረው በመግባት ሰራተኞቹ ወለሉ ላይ እንዲተኙ አስገድደዋል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎ ፖሊስ 13 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፥ ሁለት የቴሌቪዥን ስርጭት ሰራተኞች ቆስለዋል ።በኢኳዶር ለ60 ቀናት የሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰኞ እለት ከጀመረ ወዲህ ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል።አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው አንድ ታዋቂ ዘራፊ ከእስር ቤት ከጠፋ በኋላ ነው። በጓያኪል በሚገኘው የቴሌቭዥን ስቱዲዮ የተፈጠረው ክስተት በዚያው ከተማ የቾኔሮስ ቡድን አለቃ አዶልፍ ማሲያስ ቪላማር ወይም ፊቶ በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀዉ የወንጀለኛ ቡድን አለቃ ከእስር ቤት ከመጥፋቱ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ግልፅ አይደለም።

ፕሬዝደንት ኖቦአ እንደተናገሩት አሁን በሀገሪቱ ውስጥ “የውስጥ የትጥቅ ግጭት” እንዳለ እና የታጠቁ ሀይሎችን በማሰባሰብ “የተደራጁ ወንጀለኞች እና አሸባሪ ድርጅቶች ለመዋጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ከህዳር ወር ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ዳንኤል ኖቦአ በኢኳዶር ጎዳናዎች እና ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ባ ለ60 ቀናት የሚቆይ ወታደራዊ ዘመቻን በማስጀመር ጆሴ አዶልፎ ማሲያስን ፊቶ እንዲታደን ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

ፊቶ ከ2011 ጀምሮ በተደራጀ ወንጀል፣ በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት እና በግድያ ወንጀል የ34 አመት እስራት ተፈርዶበት ነበር።ከማረሚያ ቤት ሲያመልጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ 2013 ከማረሚያ ቤት አምልጦ ከሶስት ወራት በኋላ እንደገና ተይዟል፡፡

የኢኳዶር ጎረቤት የሆነችው ፔሩ አለመረጋጋትን ለመከላከል የፖሊስ ኃይል በአስቸኳይ ወደ ድንበሩ እንዲሰማራ አዛለች። ዩናይትድ ስቴትስ ከኢኳዶር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ኖቦአ እና የኢኳዶር መንግስት ጋር “በቅርበት እንደምትሰራ እና “እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ስትል ተናግራለች። ኢኳዶር ከዓለም ቀዳሚ ሙዝ ላኪ ሀገር ስትሆን በተጨማሪም ዘይት፣ ቡና፣ ካካዎ ሽሪምፕ እና አሳ ምርቶችን ወደ ውጭ ትልካለች። ውጥረቱ የተፈጠረው የአደንዛዥ እፅ ቡድኖች ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ የሚወስዱ የኮኬይን መስመሮችን ከመቆጣጠር ጋር የተያያዘ ነው ።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *