መደበኛ ያልሆነ

ጥር 1፤2016 – በከብቶች ሀሞት ከረጢት ዉስጥ ወርቅ በተደጋጋሚ የሚገኘዉ ከብቶቹ ከሚመጡበት ስፍራ የተፈጥሮ ሀብት በመኖሩ እንደሆነ ተነገረ

በበዓላት ወቅት ለእርድ በሚዉሉ ከብቶች ሀሞት ቀረጢት ዉስጥ በተደጋጋሚ ተገኘ የሚባለዉ ጉዳይ ሳይንሳዊ ምላሹ ምን እንደሆነ ብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጠይቋል፡

በተደጋጋሚ በበዓላት ወቅት ለእርድ በሚዉሉ ከብቶች ሀሞት ቀረጢት ዉስጥ ወርቅ ተገኘ የሚል ዜና መስማት እየተለመደ መጥቷል። ይህ በእንስሳቱ የሆድ እቃ ክፍል ዉስጥ የሚገኘዉ ወርቅ አንዳንዴም በከፍተኛ ገንዘብ ሲሸጥ ይሰማል፡፡ታድያ በእንስሳቶቹ ዉስጥ ተገኘ የሚባለዉ ወርቅ እንዴት ወደ ሆድ እቃቸዉ ዉስጥ ይገባል? ከገባስ በኋላ በእንስሳቶቹ ላይ የሚያመጣዉ የጤና እክል የለም ወይ? እንዴት ከአላስፈላጊ ተረፈ ምርቶች ጋር ተቀላቅሎ ሳይወገድ በሀሞት ቀረጢት ዉስጥ ይቀመጣል ? የሚሉ ጥያቄዎች የብዙዎች ናቸዉ።

የፐብሊክ ሄልዝ እና ኳራንታይን ባለሙያዉ ዶ/ር ማስሬ መሳይ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ፤ መሰል አጋጣሚዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተቱት በቀንድ ከብቶች ላይ መሆኑን ተናግረው ከብቶቹ የመጡበት አካባቢ ያለዉ የተፈጥሮ ሀብት ለዚህ አስተዋጽኦ እንዳለዉ ገልጸዋል። የቀንድ ከብቶች በባህሪያቸዉ አጫጭር ሳሮችን የሚመገቡ እና የወንዝ ዉሃን የሚጠጡ ከሆነ አሸዋ ፣ ጠጠሮ እና አንዳንዴም ወርቅን የመሰሉ ቁዶች በሀሞታቸዉ ዉስጥ እንደሚገኙ አስረድተዉናል።

ከብቶቹ ከተመገቡ በኋላም ጠጠር እና ወርቅን የመሰሉ ክብደት ያላቸዉ ቁሶች ከተመገቡት ሳር በተለየ መልኩ ሳይንሳፈፉና ወደ ጨጓራቸዉ ሳይገቡ ይቀመጣሉ ብለዋል። በጊዜ ሂደት ዉስጥም ከፈሳሽ ጋር በመቀላቀል ወደ ሀሞት ቀረጢት በማምራት እንደሚከማች ገልጸዋል።

መሰል ገጠመኞች የሚከሰቱትም አነሰ ከተባለ እስከ 10 አመታትን በቀንድ ከብቶቹ የሆድ አካል ዉስጥ ወርቁ ከተቀመጠ እና ከተከማቸ በኋላ ነዉ ብለዉናል። አመታትን በዉስጣቸው በሚቀመጥበት ወቅትም የሀሞት ቀረጢትን በመሙላት ለምግብ መፈጨት አጋዥ የሆነዉ ሀሞት እንዳይመነጭ እና ወደ ጨጓራቸዉ እንዳይሰራጭ ፤ እንዲሁም የምግብ መፈጨት ሂደታቸዉን የተዛባ እንደሚያደርገዉም አንስተዋል። አንዳንዴም የሽንት መቆጣጠር እንዳይችሉ ያደርጋቸዋልም ብለዋል።

በቅርቡ በወላይታ ዞን ጠበላ ከተማ አስተዳደር ለገና በዓል ከታረዱ ሁለት የቀንድ ከብቶች ዉስጥ 50 ግራም የሚመዝን ወርቅ የተገኘ ሲሆን 290 ሺህ ብር መሸጡም ተሰምቷል። ክስተቱ ከቀንድ ከብቶች በተጨማሪ በበግ ላይ የመከሰት እድል እንዳለ የፐብሊክ ሄልዝ እና ኳራንታይን ባለሙያዉ ዶ/ር ማስሬ መሳይ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *