መደበኛ ያልሆነ

ጥር 10፤2014-በአፍጋኒስታን በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ቢያንስ የ22 ሰዎች ህይወት አለፈ

በአፍጋኒስታን ምዕራባዊ ክፍል በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ቢያንስ ሰዎች መሞታቸውን የመንግስት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።ከዩኤስ ጂኦሎጂካል ሶሳይቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣የደረሰዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በሬክተር ስኬል ሲለካ 4.9 እና 5.3 መሆኑ ተጠቁሟል፡በአደጋዉ በርካታ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ህንጻዎች ወድመዋል፡፡

የአፍጋኒስታን የመንግስት ባለስልጣናት ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በፍርስራሹ ውስጥ ሞተው ከተገኙት መካከል አራት ህጻናት ናቸዉ ብለዋል፡፡ከ700 በላይ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሉ አክለዉ ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ትናንትና ከሰአት በኋላ የደረሰ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሁለት ሰአታት ልዩነት በኋላ ተከስቷል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዉ በቃዲስ እና ሙግር በተባሉ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ዉድመት አድርሷል፡፡

የቃዲስ አካባቢ ዋና አስተዳዳሪ መሀመድ ሳሌህ ፑርዲል በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዉ በርካታ ቤቶች መውደሙን፤ የሴቶችን እና ህጻናትን ህይወት መንጠቁን ተናግረዋል፡፡የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የተነገረ ሲሆን የነፍስ አድን ሰራተኞች በፍርስራሽ ዉስጥ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል በማጣራት ላይ ይገኛሉ።

በሚኪያስ ጸጋዬ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-ባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጲያ የህዳሴ ግድብ ከ539 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

በ2014 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባት ከ539 ሚሊየን 583 ሺ ብር በላይ መሰብሰቡን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባት ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የተሰበሰበው ገንዘብ ከሀገር ውስጥ እና በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሲሆን ገንዘቡ የተገኘው ከቦንድ ግዢ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች መሆኑን የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀይሉ አብርሀም ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።

ከ204 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ከዲያስፖራው የተገኘ ሲሆን 216 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ ከሀገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭ እና ልገሳ ተሰብስቧል። በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ብቻ የተሰበሰበው ገቢ 44 ሚሊየን ያህል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡የግድቡ ግንባት ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ከሀገር ውስጥ፣ ከውጪ እና ከቦንድ ሽያጭ ልገሳ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች ከ16 ቢሊዮን 268 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስባል፡፡

አሁን ላይ መላው ኢትዮጵውያን የህልውና ዘመቻ ላይ ቢሆንም እንኳን ለግድቡ የሚደረጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደቀጠሉ ተጠቁሟል፡፡በቅርቡ የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ በሁለቱ ተርባይነር የኤሌክትሪክ ሀይል እንሚያመነጭ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መግለፁ ይታወሳል፡፡

በትግስት ላቀዉ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-በቻይና የወሊድ መጠን ዝቅተኛ ሆኖ ተመዘገበ

በቻይና የወሊድ መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እየተመዘገበበት የሚገኝ ሲሆን የብሄራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ በዛሬዉ እለት ባወጣዉ መረጃ በ2021 ዓመት የወሊድ ምጣኔ ከ1,000 ሰዎች ወደ 7.52 ዝቅ ብሏል፡፡ ባለፈው አመት ቤጂንግ ጥንዶች እስከ ሶስት ልጆች እንዲወልዱ መፍቀዷ የወሊድ ምጣኔ የጀመረውን የቁልቁለት አዝማሚያ የሚያሳይ ሆኗል፡፡

ቻይና በ2016 ለአስርት አመታት የቆየዉን የአንድ ልጅ መውለድ ፖሊሲ በመሰረዝ የህዝብ ቁጥር ለመጨመር ብታቅድም በርካታ ጥንዶች በከተማ ዉስጥ ባለዉ የኑሮ ውድነት የተነሳ ልጆችን የመውለድ ፍላጎት እያሳዩ አይገኝም፡፡ የስታቲስቲክስ ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየዉ ከሆነ ከ1949 ጀምሮ የወሊድ ምጣኔው ዝቅተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የፒንፖይንት ንብረት አስተዳደር ዋና ኢኮኖሚስት ዡዌይ ዣንግ “የስነሕዝብ ፈተና በደንብ ይታወቃል ነገር ግን የህዝብ የእርጅና ፍጥነት ከተጠበቀው በላይ ሆኗል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡እ.ኤ.አ በ2021 በቻይና 10.62 ሚሊዮን ህጻናት እንደተወለዱ መረጃው ቢያሳይም በ2020 ከተወለዱት 12 ሚሊዮን ህጻናት ጋር ሲነጻጸር እንኳን ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-በእንግሊዝ በኮቪድ የተጠቃ ሰዉ ራሱን ማግለል ያለበት ለአምስት ቀናት ብቻ እንዲሆን ተወሰነ

በእንግሊዝ ውስጥ በኮቪድ-19 የተጠቁ ሰዎች ራሳቸዉን አግልለዉ የሚቆዩበት ዝቅተኛው ጊዜ ወደ አምስት ሙሉ ቀናት እንዲሆን ዉሳኔ ተላልፏል፡፡በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የሰራተኞች እጥረት ለማቃለል የህክምና ማስረጃዎችን በመገምገም ሰዎች ለይቶ ማቆያ ዉስጥ የሚያሳልፉበትን ቀናት ተቀንሷል።

ነገር ግን ሰዎች በተገለሉበት በአምስት እና በስድስት ቀናት ውስጥ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳ፣ የ16 እና የ17 አመት ታዳጊዎች በክትባት ማእከል በመገኘት ቫይረሱን ለመከላከል የሚስችል ክትባት መዉሰድ እንዲችሉ ተፈቅዷል፡፡

በእንግሊዝ ውስጥ ራስን ለይቶ የማቆያ ቀናት ባለፈው ወር ከ10 ወደ ሰባት ቀናት ዝቅ እንዲል ተደርጎ ነበር፡፡በዚህም ባለፈው ወር በስድስት እና በሰባት ቀናት ዉስጥ ሰዎች አገግመዉ ከቫይረሱ ነጻ የሆኑባቸዉ አጋጣሚዎች ተስተዉሏል፡፡

ራስን በማግለል ህግ መሰረት፣ ሰዎች ምልክቱ ከሚታይባቸዉ ወይም በቫይረሱ መያዛቸዉ በምርመራ የተረጋገጠበት ቀን ሳይቆጠር ከሚቀጥለው ቀን ጀምሮ አንስቶ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ራሳቸዉን ያገላሉ፡፡

በሚኪያስ ፀጋዬ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-በኦሮሚያ ክልል የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 11 የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ በርካታ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸው ተነግሯል።

ከጉጂ ዞን ወደ ምእራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ደዴሳ ቀበሌ በመግባት የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲዘጋጁ የነበሩ 11 የሽብርተኛው ቡድን ታጣቂዎች በፀጥታ አካላት እና በማህበረሰቡ ትብብር በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የቡድኑ አባላት በተጨማሪ ስድስት ክላሽንኮቭ ፣ ሶስት የጦር መሳሪያ እና 180 የተለያዩ ጥይቶች ይዘው መገኘታቸው የምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ኢንስፔክተር ሁሴን ከድር ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል

በሳምራዊት ስዩም

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-የጥምቀት በዓል ሲከበር ለአደጋ ስጋት የሆኑ አሰራሮች መወገድ አለባቸው ተባለ፡፡

የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ አደባባዮችን ፣መንገዶችን እና ታቦት ማደሪያ ስፍራዎችን ለማሳመር ተብለው የሚሰሩ ስራዎች ለአደጋ ስጋት እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እና በባለሙያ መታገዝ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ከብስራት ሬድዮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንደተናገሩት ከሶስት ዓመት በፊት አዲሱ ገበያ አካባቢ አራት ወጣቶች ታቦታቱ የሚሄዱበትን ሰረገላ ሲገፉ ፤ሰረገላው ከረገበ ኤሌክትሪክ ጋር ተገናኝቶ የወጣቶቹ ህይወት ማለፉን ያስታወሱ ሲሆን አሁንም በከተማዋ ላይ እየተሰሩ ያሉ የጥምቀት በዓል ስራዎች አደጋን ታሳቢ ተደርገው በጥንቃቄ እና ባለሙያ በታከለበት መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡

እንደ አቶ ንጋቱ ማብራሪያም ጊዜያዊ ኤሌክትሪክ በሚዘረጋባቸው የታቦታ ማደሪያ ድንካኖች እና መድረኮች ሲዘጋጁ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ አብራርተዋል፡፡የኤሌክትሪክ ገመዶች ከሰው ቁመት በላይ ማድረግ ፣ አንጸባራቂ ምልክቶች እና ኤሌክትሪክ የሚዘረጋባቸው እንጨቶችም በጥልቅ በተቆፈረ ጉድጋድ መቀበር እንዳለባቸው እንስተዋል፡፡

ታቦታ በሚያልፉበት መንደሮች የታቦታት ማጀቢያ ሰረገላዎች ከረገቡ ኤሌክትሪኮች መስመሮችም ጋር እንዳይገናኙ ማረጋገጥ የረገቡም ካሉ አስቀድመው ለኤሌክትሪክ ሀይል ማሳወቅ እና መሰራት እንዳለባቸው አቶ ንጋቱ አስረድተዋል፡፡በበዓሉ እለትም የጸበል አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ ጥንቃቄ እንዳይለይ ኮሚሽኑ ያሳሰበ ሲሆን የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ከቤተክርስቲያናት ጋር በመነጋገር ታቦታት ማደሪያ ቦታዎች ላይ አብረው የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየሠሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

በትግስት ላቀው

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት 29 ዳቦ ቤቶች ግራም ቀነሰው ሲሸጡ በመገኘታቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል

በአዲስ አበባ ከተማ ከ2800 በላይ ዳቦ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ከመንግስት ድጎማ ውጪ ሆነው ራሳቸው የስንዴ ግዢ በመፈጸም ዳቦን ጋጋረው እያቀረቡ ይገኛል።ሸገር ዳቦ በመንግስት በሚደረግለት ድጋፍ ለህብረተሰቡ ዳቦን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው።

ዳቦ ቤቶች ስንዴን በራሳቸው ወጪ እያቀረቡ በመሆኑ የዳቦውን መጠን የመወሰን መብት ቢኖራቸውም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ዳቦ ቤቶቹ ባሳወቁት እና በለጠፉት የግራም መጠን ዳቦ እያቀረቡ መሆናቸውን ያጣራል ያሉት በቢሮው የኮሚኒኬሽ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሚኤሶ ናቸው።በዚህ መሰረት ባለፉት ስድስት ወራት በስነ ልክ ህግ መሰረት ህጉን ተላልፈው የተገኙ 29 ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን አቶ ዳንኤል በተለይ ለብሰራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው 29 ዳቦ ቤቶች መካከል ሰባቱ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው የተቀሩት ላይ ደግሞ አስተዳዳራዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አማካኝነት የተጀመረው የዳቦ ፋብሪካ በሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን የግብአት እና የአቅርቦት የሙከራ ስራ ላይ ይገኛል።

ሸገር ዳቦ እያቀረበበት ያለው የዋጋ ተመን ከገበያው አንፃር የማያዋጣ እንዲሁም የስንዴ እጥረት ችግር አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም ይህንን ታሳቢ በማድረግ የዋጋው ማስተካከያ እና መንግስት ለማህበረሰቡ ከሚያቀርበው 165 ሺህ ኩንታል ዱቄት ውስጥ 60 ሺህ ኩንታሉን ለሸገር ዳቦ በመስጠት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርብ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ አቶ ዳንኤል ጨምረው ለብሰራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በቤተልሄም እሸቱ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-በኢትዮጲያ የፀረ ኤች አይቪ ኤድስ መድኃኒት ከሚወስዱት ውስጥ 24 በመቶ ያህሉ አቋርጠዋል ተባለ

በአሁን ሰዓት በኢትዮጲያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት መጠን 3.4 በመቶ እንደደረሰ ተነግሯል ፡፡እንደ አዲስ አበባ ያሉ በርካታ ህዝብ የሚበዛባቸው እና ከፍተኛ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ የሚያስተናግዱ አከባቢዎች ደግሞ ለቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት ይሆናሉ ሲሉ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ይርጋ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡

የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ከ 1 በመቶ በላይ ካለፈ ከፍተኛ የጤና ስጋት መሆኑን ያሚያመለክት ነው ፤ ያሉት ሃላፊው ይህ ስርጭት በአሁን ሰዓት ከ3 ከመቶ በመሻገሩ ከፍተኛ የጤና ስጋት ተብሎ እንዲፈረጅ አድርጎታል ሲሉ በተጨማሪነት ተናግረዋል ፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒትን እና የህክምና ክትትል የሚያደርጉ ተጠቂዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ አቶ ዳንኤል ተናገረዋል። በሌላ በኩል ባለፈው አንድ ዓመት የፀረ ኤች አይቪ ኤድስ መድኃኒት ከሚወስዱት ውስጥ 24 በመቶ የሚሆኑ ህክምናቸውን እንዳቋረጡ አስታውቀዋል ፡፡

ህክምናቸውን እንዲያቋርጡ ያደረገው እና በምክንያትነት የሚቀመጠው ቀዳሚ ጉዳይ ኮሮና ተህዋስ ወረርሽኝ ሲሆን የታካሚዎቹ ቸልተኝነትም ሌላው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል ፡፡

ናትናኤል ሀብታሙ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-የዓለማችን 10 ሀብታም ሰዎች ሀብት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በእጥፍ ጨምሯል ተባለ

ወረርሽኙ የዓለማችንን ሀብታሞች እጅግ ያበለፀገ ቢሆንም በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት እንዲኖሩ አድርጓል ሲል ኦክስፋም በጎ አድራጎት ድርጅት ገልጿል።ይህዉ ወረርሽኝ በየቀኑ ከ21,000 በላይ ሰዎች ሞት ምክንያት ስለመሆኑ እና እኩልነትን ማስፈን ተገቢ መሆኑን ኢክስፋም በዛሬዉ እለት ባወጣዉ ሪፖርት አስታዉቋል።

የዓለማችን 10 በጣም ሀብታም ሰዎች ከመጋቢት 2020 ጀምሮ የጋራ ሀብታቸው በእጥፍ መጨመሩን ኦክስፋም በዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ስብሰባ መጀመሪያ ላይ ስለ ዓለም አቀፍ እኩልነት ባወጣዉ ሪፖርት ላይ አመላክቷል፡፡

የፎርብስ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የዓለማችን 10 ሀብታም ሰዎች የሚባሉት የቴስላ ባለቤት ኢሎን ማስክ፣የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ፣ በርናርድ አርኖት እና ቤተሰቡ፣ ቢል ጌትስ፣ ላሪ ኤሊሰን፣ ላሪ ፔጅ፣ ሰርጌ ብሪን፣ የፌስቡኩ ማርክ ዙከርበርግ፣ ስቲቭ ቦልመር እና ዋረን ቡፌት ናቸው።

በአጠቃላይ ሀብታቸው ከ 700 ቢሊዮን ዶላር ወደ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ሲጨምር በመካከላቸው ግን ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ ለአብነትም የማስክ ሀብት ከ1,000 በመቶኛ በላይ የጨመረ ሲሆን የቢል ጌትስ የሀብት መጠን በአንጻሩ በ30 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2014-በባንግላዴሽ ለ20 ዓመታት በሆድ ዉስጥ የተረሳ መቀስ ከአንዲት ሴት እንዲወጣ ተደረገ

ለ20 አመታት በሆድዋ ላይ የማያቋርጥ ህመም ስታሰቃይ የኖረችው ባንግላዲሽያዊት ሴት በቀዶ ህክምና ወቅት ሰውነቷ ውስጥ የተረሳ መቀስ ተገኝቷል፡፡የ55 ዓመቷ ባቸና ኻቱን በ2002 በቹአዳንጋ በሚገኝ ክሊኒክ የሐሞት ጠጠርን የማስወገድ ቀዶ ጥገና ከተደረገላት ጊዜ ጀምሮ የማያቋርጥ የሆድ ህመም ይዟት ነበር። ከህክምናው ሁለት ቀናት በኃላ ሆዴ ውስጥ ህመም ይሰማኛል ስትል ወደ ክሊኒኩ ትመለሳለች፡፡

የቀዶ ጥገና ህክምናዉን የመሩት ሃኪም ስጋቷን ውድቅ በማድረግ ህመሙ የተለመደ እንደሆነ እና መጨነቅ እንደሌለባት ቢገልጹላትም ይህ ግን ስህተት ነበር፡፡የሆድ ህመሟ ተባብሶ በመቀጠሉ ከአንዱ ዶክተር ወደ ሌላ ሐኪም በመሄድ ህክምናዋን ለመከታተል ብትሞክርም የሚታይባትን የህመም ምልክት ለመቅረፍ በሐኪሞች መድኃኒት ሲታዘዝላት ቆይታለች፡፡

ከቅርብ ቀናት ወዲህ የሆድ ህመሟ ለመቋቋም የሚቸግር አይነት መሆኑን ተከትሎ በአንድ በዶክተር ምክር በተደረገላት የኤክስሬይ ምርመራ ከ20 አመታት በፊት በሀሞት ከረጢት ቀዶ ጥገና ህክምና የተረሳው መቀስ ተገኝቷል፡፡በተደረገላት ህክምና መቀሱን ማዉጣት የተቻለ ሲሆን በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ ተነግሯል፡፡

በስምኦን ደረጄ