መደበኛ ያልሆነ

ጥር 19፤2015-የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከላቭሮቭ ጋር ስለ ዩክሬን ጦርነት ተወያዩ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ትናንት ሀሙስ በሁለትዮሽ ግንኙነት እና በዩክሬን ግጭት ዙሪያ ተወያይተዋል።የዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ የኤርትራው ፕሬዝዳንት “አለም አቀፍ የዋልታ የመሆን ስርዓትን ለመፍጠር የነበረው ቅዠት ሙሉ በሙሉ ከሽፏል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዓለምን ለአደጋ ያጋለጠውን የቅኝ ግዛት እና የግዛት ታሪክን ለመቋቋም እና ለመዋጋት የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል ።የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ውይይቱ “በዩክሬን ስላለው ጦርነት ተለዋዋጭነት” እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር ላይ ነበረ ሲሉ ተናግረዋል።

“ውይይቶቹ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ተለዋዋጭነት እና በሃይል፣ በማዕድን ማውጫ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች ላይ ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነበር” ሲሉ የማነ በትዊተር ገጻቸዉ ላይ አስፍረዋል።እ.ኤ.አ በመጋቢት 2022 የሞስኮ ዩክሬን ጦርነት ተከትሎ ሩሲያን ለማውገዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔ በመቃወም ድምጽ የሰጠች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ኤርትራ መሆኗ ይታወሳል።

ላቭሮቭ ኤርትራ የገቡት በስድስት ወራት ውስጥ ባደረጉት ሁለተኛ የአፍሪካ ጉብኝታቸው የመጨረሻ ዙር ሲሆን ወደ አንጎላ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢስዋቲኒ አቅንተዋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 17፤2015-በጌድኦ ዞን በእሳት አደጋ የሶስት ህፃናት ህይወት አለፈ

👉 በአደጋው ወቅት የህፃናቱ ወላጆች ለቅሶ ቤት ለአዳር መሄዳቸው ተሰምቷል

በጌድኦ ዞን ገደብ ወረዳ ወረቃ ጫቤሳ ቀበሌ በድንገት በተከሰተ የእሳት አደጋ የሶስት ህፃናት ህይወት ማለፉን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

አደጋው የተከሰተው ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከለሊቱ 7:00 ሰዓት ሲሆን እሳቱ የተነሳው ከአንድ ግለሰብ ሱቅ ውስጥ መሆኑን እና መንስኤውም የኤሌክትሪክ ሽቦ ኮንታክት በማድረጉ እንደሆነ ተገልጿል።

በወቅቱ ህይወታቸዉ ያለፈዉ ሶስቱ ህፃናት ላይ በር ተቆልፎባቸዉ እንደነበርና ቤተሰቦቻቸዉ ጎረቤት በነበረረ ለቅሶ ለማደር በሄዱበት አጋጣሚ አደጋው አጋጥሟል።

በደረሰዉ የእሳት ቃጠሎ ከሶስቱ ህፃናት ህልፈት በተጨማሪ ተያይዘዉ የተገነቡ የንግድ ሱቆች ወደመዋል።በቃጠሎዉ በሰው ላይ ከደረሰው አደጋ በተጨማሪ የንብረት ዉድመት በተመለከተ ለጊዜዉ አለመታወቁን ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በሳምራዊት ስዩም

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 17፤2015-ኮንቴነር ውስጥ ድብብቆሽ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት የነበረው የኢንዶኔዥያ ዜግነት ያለው ታዳጊ ራሱን ማሌዢያ ውስጥ አገኘው

ፋሂም ተብሎ የሚጠራው የኢንዶኔዥያ ዜግነት ያለው ታዳጊ በሀገሪቱ የወደብ ከተማ ከጓደኞቹ ጋር ኮንቴነር ውስጥ እየገቡ ድብብቆሽ ሲጫወት ነበር።ከ11 እስከ 15 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የተገመተው ታዳጊ ታዲያ በአንዱ ኮንቴነር ውስጥ ገብቶ ጓደኞቹ ሲቆዩበት እንቅልፍ ሸለብ ያደርገዋል።

ዘ ዴይሊ ስታር እንደዘገበው የገባበት ኮንቴነር ተቆልፎ በመርከብ ተጭኖ ከኢንዶኔዥ ወደ ማሌዥያ ጉዞ ይጀምራል።ከስድስት ቀናት የባህር ላይ ጉዞ በኃላ ያለ ምግብና ውሃ በህይወት መትረፉ ፋሂም እድለኛው ታዳጊ በሚል ስሙ እየተነሳ ይገኛል።

የማሌዢያ የወደብ ሰራተኞች በምግብና ውሃ እጦት የተዳከመውን ታዳጊ የህክምና ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረጋቸው ተሰምቷል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 17፤2015-ጀርመን እና አሜሪካ የጦር ታንክ ወደ ዩክሬን ለመላክ ተስማሙ

ከወራት እምቢተኝነት በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመን ታንኮች ወደ ዩክሬን ለመላክ መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል። ወሳኔው ዩክሬን በጦር ሜዳ ላይ ለሚኖራት ውጊያ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ቢያንስ 30 “ኤም 1 አብራምስ” የተሰኙ ታንኮችን ለመላክ ማቀዱን ያስታውቃል ተብሎ ይጠበቃል። የጀርመን መራሂተ መንግስት ኦላፍ ሾልስም ቢያንስ 14 ሊኦፓርድ 2 ታንኮች ለመላክ መወሰናቸውን ተዘግቧል። በአሜሪካ የሩስያ አምባሳደር ውሳኔውን “ሌላ ግልጽ የጦርነት ቅስቀሳ” ሲሉ ወቅሰዋል።

የዩክሬን የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው እንዲህ አይነት ድጋፍ ሩሲያ ከግዛታችን ለቃ እንድትወጣ ሊረዳቸው እንደሚችል ተናግረዋል ። እስካሁን ድረስ አሜሪካ እና ጀርመን ታንኮቻቸውን ወደ ዩክሬን ለመላክ ውስጣዊ እና ውጫዊ ግፊትን እንደተቋቋሙ ተጠቁሟል።

ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን ታንክ ማቅረቡ ጉዳዩን እንደማይለውጥ እና ምዕራባውያን በሚደረገው የጦር ሜዳ ትግል ኪየቭ ሞስኮን ልታሸንፍ ትችላለች በሚለው የማታለል ውሳኔያቸው ይጸጸታሉ ስትል ገልጻለች። በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ በዛሬው እለት በቴሌግራም ገፃቸው ባጋሩት መረጃ “ዩናይትድ ስቴትስ ታንኮችን ለማቅረብ ከወሰነች የመከላከያ መሳሪያ ለማቅረብ ነው በሚል ክርክር ማመካኘት በእርግጠኝነት አይቻልም በሩሲያ ፌዴሬሽን ላይ ሌላ ግልጽ የጦርነት ቅስቀሳ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 16፤2015-በትላንትናው እለት በተከሰቱ ሶስት የእሳት አደጋዎች በ10 ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ የተገመተ ንብረት ወድሟል

👉 የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ለተጨማሪ አገልግሎት የተከራየው ህንጻ ውድመት ደርሶበታል

በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ትላንት ጥር 15 ቀን ሶስት የእሳት አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም 10 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የእሳት አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ትላንት ከቀኑ 10:46 በሸገር ከተማ ቡራዩ በሹፋን ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ300 ሺህ ብር በላይ የተገመተ ንብረት ወድሟል።

በሌላ በኩል ምሽት 3:55 በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አስኮ መነሀሪያ በህዝብ ማመላለሻ አዉቶቢስ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 1 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ወድሟል።

እንደዚሁም ምሽት 4:58 ባለ 7 ወለል ህንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ1.6 ሚሊየን ብር በላይ የተገመተ ንብረት ሲወድም በ10 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ ንጋቱ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል። ከተጎጂዎቹ መካከል ሶስቱ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ናቸዉ።

የእሳት አደጋዉ ከህንጻዉ ምድር ቤት የተነሳ ሲሆን እሳቱ እስከ ሁለተኛ ፎቅ ድረስ ጉዳት አድርሷል። ህንጻዉ ለለሚ ኩራ ክፍለ አስተዳደር ለተጨማሪ የቢሮ አገልግሎት የተከራየ ሲሆን ስራ ለመጀመር በሂደት ላይ የነበረ መሆኑም ታውቋል።

ሶስቱንም የእሳት አደጋዎች ለመቆጣጠር 8 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪና 2 አምቡፑላንስ ከ65 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር የተሰማራ ሲሆን አደጋዎቹን ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት ከ250 ሚሊየን ብር በላይ የተገመተ ንብረት ማዳን ተችሏል።

በትግስት ላቀው

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 12፤2015-የፔሩ ዋና ከተማ ሊማን ለመቆጣጠር የሞከሩ የተቃዋሚ ሰልፈኞችን ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ በተነ

በፔሩ ዋና ከተማ ሊማ የተቃዋሚ ሰልፈኞች ፕሬዚዳንት ዲና ቦሉዋርት ከስልጣን እንዲወርዱ ለመጠየቅ ወደ ከተማዋ በገቡበት ወቅት ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ለመበተን ሞክሯል፡፡ሰልፈኞቹ በትላንትናዉ ዕለት በሊማ ታሪካዊ ዳውንታውን አካባቢ ኮንግረሱን ጨምሮ ቁልፍ የመንግስት ህንጻዎች ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ዉስጥ ገብተዋል፡፡

ለበርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቅርብ ከሆነው ህንፃ ላይ እሳት መቀስቀሱን ተከትሎ ሰዎች ንብረታቸውን ለማውጣት ሲጣደፉ የሚያሳዩ ምስሎች ተጋርተዋል። የፔሩ ብሄራዊ ፖሊስ ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲርቁ ጠይቋል።

ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር የድመት እና የአይጥ ሁኔታን በአደባባይ ሲያሳዩ የነበረ ሲሆን አንዳንድ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር በመጋፈጥ ድንጋይ ሲወረውሩ በአጸፋዉ አስለቃሽ ጭስ ተተኩሷል፡፡ፖሊስ በተቃውሞው ወደ 3,500 የሚጠጉ ሰዎች እንደተሳተፉ ቢገልጽም ሌሎች ሪፖርቶች ግን ቁጥሩ ከተገመተው እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በተቃውሞ ለተገደሉት 50 የሚጠጉ ሰዎች ፍትህ እንፈልጋለን ፕሬዝዳንቷ ቦልዋርቴ ስልጣን እስክትለቅ ድረስ ሰልፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።በትላንትናዉ ተቃዉሞ በአጠቃላይ 22 የፖሊስ መኮንኖች እና 16 ሲቪሎች መቁሰላቸዉን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቪሴንቴ ሮሜሮ ፈርናንዴዝ ተናግረዋል፡፡

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 12፤2015-ከቆሻሻ የሚሰራ ጭስ አልባ ከሰል በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ መምህር ተመረተ

በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ፈቃዱ እንግዳ ለብስራት ራዲዮ እንደተናገሩት ፤ ከቆሻሻ የሚሰራ ጭስ አልባ ከሰል ማምረት መቻሉን ገልፀዋል።

ምርቱ ከፕላስቲክ ፣ ብርጭቆ እና የብረት ተረፈ ምርት ዉጪ የመጸዳጃ ቤት ፣ የእንስሳት ጽዳጅ እንዲሁም ማንኛውን ቆሻሻ ለምርቱ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል። በ 2012 ዓ.ም የተጀመረዉ ፕሮጀክቱ ላለፉት ሶስት አመታት የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዉበታል።

ምርቱ በገበያ ላይ ካለዉ የእንጨት ከሰል የተሻለ መሆኑን ያነሱት የፕሮጀክቱ ባለቤት ፤ ከዚህ ቀደም ከቆሻሻ ከሚመረተዉ ጭስ አልባ ከሰል በተለየ ለማህበረሰቡም ሆነ ለተጠቃሚዎች አመቺ በሆነ መጠን ተዘጋጅቷል።

ሆኖም ይህን ፕሮጀክት ወደ ተግባር ለመለወጥ እና በስፋት ለማምረት ግን አመቺ የስራ ቦታ ማጣት እና የማሽነሪ አለመሟላት እንዳጋጠማቸዉ ገልጸዋል።

የስራ ቦታን በሚመለከትም ከከተማ አስተዳደሩ ቦታ የተጠየቀ ቢሆንም ፤ አስተዳደሩ ቦታ የሚያቀርበዉ እንደ አንድ ባለሃብት ተመዝገበዉ አስፈላጊ መስፈርቱን ኳሟሉ እንደሆነ እንደተነገራቸዉ መምህሩ ገልፀው ይህን ለሟሟላት ግን አቅሙ እንደሌላቸዉ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱን ለመስራት በደብረማርቆስ ከተማ የመጸዳጃ ቤት ቆሻሻ መጣያ አመቺ ቦታ አለመኖሩን አንስተዋል። በአዲስአበባ (ቆሼ) በተከሰተዉ አደጋ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች መነሻ ምክኒያት እንደሆናቸዉ መምህር ፈቃዱ ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2015-በአዲስ አበባ ከመስቀል አደባባይ ቀጥሎ ትልቁ የህዝብ አደባባይ ሊገነባ ነው

በዛሬው እለት 14 ሺህ 400 ሔክታር መሬት ላይ ያርፋል የተባለውና በ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የለሚ ፖርክ ግንባታ በይፋ ተጀምሯል።

ከመስቀል አደባባይ ተጨማሪ በመዲናዋ ትልቁ የህዝብ አደባባይ ይሆናል የተባለው ይኸው ፕሮጀክት ወጪው በመንግስት እና በግል ባለሀብቶች የሚሸፈን ነውም ተብሏል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፕሮጀክቱ በ10 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

የፓርኩ ግንባታ መጀመር ለ 1 ሺህ 100 ሰዎች የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ለ 400ዎቹ ቋሚ የስራ እድል እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

ፖርኩ የመኪና ማቆምያ፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ጂምናዝየሞችን፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የህዝብ መሰባሰቢያ ስፍራ (public space)፣ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ፣ የሰርግና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውል መናፈሻ፣ ሱፐርማርኬት፣ የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች፣ መጽሀፍት የማንበቢያ ስፍራና የመሳሰሉት ይኖሩታል፡፡

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 9፤2015-የቻይና ህዝብ ቁጥር ከ60 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀነሰ

በ 60 ዓመታት ውስጥ የቻይና ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀነሰ ሲሆን ፣ ብሔራዊ የወሊድ መጠን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ከ 1,000 ሰዎች 6.77 ያህሉ ብቻ ይወልዳሉ፡፡እ.ኤ.አ በ 2022 የቻይና ህዝብ ብዛት 1.41 ቢሊዮን ሲሆን ከ 2021 ዓመት በ 850 ሺኅ ቀንሷል።

የቻይና የወሊድ መጠን ለዓመታት እያሽቆለቆለ የነበረ ሲሆን ይህንን አዝማሚያ ለመቀየር በርካታ ፖሊሲዎች እየተተገበሩ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከሰባት ዓመታት በፊት የአንድ ልጅ ፖሊሲ ቢወገድም “አሉታዊ የህዝብ ቁጥር ዕድገት ዘመን” ሲሉ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ 2022 የወሊድ መጠን በ 2021 ከነበረዉ 7.52 ቀንሷል ሲል የቻይና ብሄራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ ይፋ አድርጓል።በአንፃሩ በ2021 በዩናይትድ ስቴትስ ከ1,000 ሰዎች 11.06፣ በእንግሊዝ ደግሞ 10.08 በአማካይ እንደሚወልዱ ተመዝግቧል። ቻይናን በዓለም በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ ብትሆንም በተፎካካሪዋ ሕንድ በተመሳሳይ ዓመት 1ሺህ ሰዎች መጠን 16.42 ነበር።

በቻይና ባለፈው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሟቾች ቁጥር መጠን ከዉልደት ጨምሯል፡፡በሀገሪቱ ከ1976 ወዲህ ከፍተኛውን የሞት መጠን አስመዝግባለች የተመዘገበ ሲሆን በ1,000 ሰዎች 7.37 ሞት ሲመዘገብ ካለፈው አመት 7.18 የጨመረ ሆኗል፡፡

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ጥር 8፤2015-በጎባ ከተማ ለ39 ግለሰቦች በህገወጥ መልኩ መሬት ሲያከፋፍሉ የነበሩ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞች በእስራት እና በገንዘብ ተቀጡ።

በባሌ ዞን ጎባ ከተማ ሆዳ መውጫ በተባለ አካባቢ የሚገኘውን የመንግስትን መሬት በመሸንሸን በህገ ወጥ መንገድ ለተጠቃሚዎች ያስተላለፉ ስድስት የጎባ ከተማ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞች በእስራት እና በገንዘብ መቀጮ መቀጣታቸውን የባሌ ዞን ፖሊስ አስታውቋል።

አንደኛ ተከሳሽ አለማየሁ አበራ የጎባ ከተማ መሬት አስተዳደር መሀንዲስ እና ሌሎች አምስት ግብረአበሮች ጋር በጋራ በመሆን በፈጸሙት የሙስና ወንጀል በእስራት ሊቀጡ የቻሉት።

በጎባ ከተማ ሆዳ መውጫ ብሎክ 11 በተባለው ቦታ 5.1 የሆነውን ሄክታር መሬት እያንዳንዱን ከ40 እስከ 48 ሺ ብር ለ39 ግለሰቦች በህገ ወጥ መንገድ ሲያከፋፍሉ በተገኘው መረጃ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጎባ ከተማ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ እና ፍትህ ማሰጠት ዲቪዥን ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ቦራ አማን ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

እነዚህ ግለሰቦች ስልጣናቸውን በመጠቀም ህብረት በመፍጠር የፈጸሙት ወንጀል በመረጋገጡ አንደኛ ተከሳሽ በ17 አመት እስራት እና በ440 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ ሌሎች ሶስት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ 14 አመት እስራት እና በ80 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ የተቀጡ ሲሆን አምስተኛ ተከሳሽ በ6 አመት እና በ7 ሺ ብር እንዲሁም ስድስተኛ ተከሳሽ በ9 ወር እስራት እና በ8 መቶ ብር እንዲቀጡ መወሰኑን ረዳት ኢንስፔክተር ቦራ አማን ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በሳምራዊት ስዩም