መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 – ኢኳዶር ቀንደኛ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ከእስር ቤት ካመለጠ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች

ኢኳዶር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች ሲሆን “እጅግ አደገኛ” የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ከከፍተኛ የጸጥታ እስራት ቤት ማምለጡን ተከትሎ ሁከት በተከሰተባት ሀገር ውስጥ በበርካታ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ አለመረጋጋት ተፈጥሯል።ከህዳር ወር ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ዳንኤል ኖቦአ በኢኳዶር ጎዳናዎች እና ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ባ ለ60 ቀናት የሚቆይ ወታደራዊ ዘመቻን በማስጀመር ጆሴ አዶልፎ ማሲያስን ፊቶ እንዲታደን ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በየቀኑ ከሰዓት እላፊ ገደብ ጋር እንደሚተገበር ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ፕሬዝዳንት ኖቦ በኢንስታግራም ላይ በለቀቁት ቪዲዮ አሸባሪዎች ካሏቸዉ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋዋሪዎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ተግባራቸውን ለመወጣት “ሁሉንም የፖለቲካ እና የህግ ድጋፍ” ለወታደራዊዉ ኃይል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

ፊቶ ከ2011 ጀምሮ በተደራጀ ወንጀል፣ በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት እና በግድያ ወንጀል የ34 አመት እስራት ተፈርዶበት ነበር።ከማረሚያ ቤት ሲያመልጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ 2013 ከማረሚያ ቤት አምልጦ ከሶስት ወራት በኋላ እንደገና ተይዟል፡፡በሺዎች የሚቆጠሩ የጸጥታ ሃይሎችን ባሳተፈ ኦፕሬሽን ፊቶ ባለፈው ነሃሴ የፕሬዝዳንት እጩ ፌርናንዶ ቪላቪሴንሲዮ መገደሉን ተከትሎ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚገኝ እስር ቤት ተዘዋውሯል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 -የልደት በዓልና የቤዛ ኩሉ ሥነሥርዓት በሰላም ተጠናቀቀ

በላሊበላ የሚከበረዉ የልደት እና የቤዛ ለኩሉ ሥነሥርዓት በሰላም መጠናቀቁን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል። የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል እና የላሊበላ ልዩ መገለጫ የሆነው የቤዛ ኩሉ ሥነሥርዓት በብፁዓን አባቶች፣ በካህናትና ምዕመናን ታጅቦ መከወኑን ነዉ ጣቢያችን የሰማዉ። በሥነሥርዓቱ ላይ የዉጪ ቱሪስቶች መታደማቸዉንም ለማወቅ ችለናል።

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 -ሼህ አብዱ ያሲንን በመግደል የሚጠረጠረው መሀመድ ሽኩር አበባው ይፈለጋል ተባለ

ግለሰቡ እጁን እንዲሰጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል። ተጠርጣረው ያለበትን የሚያውቅ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር አዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል።

አዲስ አበባ ፖሊስ በሼህ አብዱ ሞት የተሠማውን ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው እና ለእምነቱ ተከታዮች መፅናናትን ይመኛል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀሉን ፈፃሚ በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትልና የምርመራ ቡድኖችን አዋቅሮ ክትትሉን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የመኖሪያ አድራሻው ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ወረዳ 14 ነዋሪ የሆነው ሟቹ ያሳድጉት የነበረው መሀመድ ሽኩር አበባው ሼህ አብዲ ያሲንን በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ይፈለጋል።ስለሆነም መሀመድ ሽኩር አበባው ያለበትን የሚያውቅ ሆነ ማንኛውም መረጃ ያለው በስልክ ቁጥር 011-1-11-01-11 ወይም በነፃ ስልክ ቁጥር 991 መረጃ በመስጠት እንዲተባበር አዲስ አበባ ፖሊስ ያስታውቃል፡፡

በወንጀል የተጠረጠረ ግለሠብን መደበቅ ሆነ እንዲያመልጥ መተባበር የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ያስታውቃል።

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 -ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች በደህንነት ፍተሻ የተነሳ ከበረራ ታገዱ

የዩናይትድ ስቴትስ የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ብዛታቸውን 171 የሆኑ ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች ደኅንነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ከበረራ ተገለው  እንደሚቆዩ አስታውቋል። የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር በአላስካ አየር መንገድ የአውሮፕላን ፍንዳታ አርብ እለት ከደረሰ በኋላ አውሮፕላኖቹ ሲፈተሹ ቆይተዋል።የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የህዝብ ደህንነት መጠበቅ ነው ብሏል።

የቦይንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴቭ ካልሁን ለሰራተኞቹ እንደተናገሩት “የኩባንያው ትኩረት መሆን አለበት” ብለዋል። ዋና ዋና የአሜሪካ አየር መንገዶች በደርዘን የሚቆጠሩ አውሮፕላኖችን ከደህንነት ጋር በተያያዘ ከበረራ እንዲቆሙ ማድረጋቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች በረራ እንዲሰረዝባቸው ምክንያት ሆኗል።ጉዳት የደረሰባቸውን አውሮፕላኖች አቁመናል፣ ደህና መሆናቸውን እስኪያረጋግጥ ድረስ መሬት ላይ እንዳሉ ይቆያሉ” ሲል የአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደር በትላንትናው እለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ቦይንግ በበኩሉ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የፊታችን ማክሰኞ የሁሉም ሰራተኞች የደህንነት ስብሰባ እንደሚያካሂድ ገልጿል።

እንዲህ አይነት ከባድ አደጋዎች ሲከሰቱ የችግሩን መንስኤዎች ለመረዳት እና መፍትሄ ለመስጠት ከደንበኞቻችን እና ተቆጣጣሪዎቻችን ጋር በግልፅ መስራት እና እንደገና እንዳይከሰቱ ለማድረግ ለእኛ ወሳኝ ነው” ሲሉ ካልሁን ተናግረዋል። የአውሮፕላኖቹ ከበረራ መታገድ በዋነኛነት በአሜሪካ በረራዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በአሜሪካ ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች በዩናይትድ አየር መንገድ እና በአላስካ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ።

የቱርክ አየር መንገድ፣ የፓናማ ኮፓ አየር መንገድ እና ኤሮሜክሲኮ ተመሳሳይ ሞዴል ያላቸውን አውሮፕላኖች ለምርመራ በሚል አውሮፕላኖቹን ከበረራ አግደዋል። አላስካ አየር መንገድ 65 አውሮፕላኖችን ያገደ ሲሆን በትላንትናው እለት 163 በረራዎችን ወይም 21 በመቶውን የአየር መንገዱን በረራዎች ሰርዟል።ወደ 25 ሺ የሚጠጉ ሰዎች በበረራው መሰረዝ ተጎድተዋል። አየር መንገዱ አንዳንድ አውሮፕላኖቹን ከበረራ መታገዳቸውን ተከትሎ የሚፈጠረው የጉዞ መስተጓጎል ቢያንስ እስከ ሳምንቱ አጋማሽ ድረስ እንደሚቀጥል ተናግሯል።ዩናይትድ አየር መንገድ 79 አውሮፕላኖችን ማገዱን እና እሁድ እለት ወደ 180 የሚጠጉ በረራዎችን መሰረዙን አስታውቋል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 -ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ሞተር ሳይክሎችና ከ2 ቶን በላይ የሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ማሽከርከር የማይችሉባቸው መንገዶች ይፋ ሆነዋል

የአዲስ አበባ ፖሊስ ሞተር ሳይክሎችና ከሁለት ቶን በላይ የሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ማሽከርከር የማይችሉባቸው መንገዶችን ይፋ አድርጓል።ክልከላውን በሚጥሱ አሽከርካሪዎች ላይም ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቋል።

የአዲሰ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ሰሞኑን ለሞተር ሳይክሎችና ከሁለት ቶን በላይ ለሆኑ ተሽክርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶችን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ክልከላው ከቦሌ በኦሎምፒያ መስቀል አደባባይ፣ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት፣ አራት ኪሎ በሁለቱም አቅጣጫ ሲሆን፤ የትራፊክ ፍሰቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው የትራፊክ ምልክቶች መተከላቸውንም መረጃው ጠቅሷል።

አዲስ የተተከሉት ምልክቶችና ማመልከቻዎች ከ2 ቶን በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች እና ሞተር ሳይክሎችን የሚከለክሉ በመሆኑ፤ በተጠቀሰው መንገድ ከዛሬ ጀምሮ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ አውቀው ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።

የተተከሉ ምልክቶችን ማክበር ከአሽከርካሪዎቹ እንደሚጠበቅ እና ይህንኑ ለማረጋገጥ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገልጿል።የተሽከርካሪ ባለንብረቶችም ሆኑ አሽከርካሪዎች ይህን ተገንዝበው ለሕጉ መከበር ግዴታቸውን እንዲወጡ ፖሊስ አሳስቧል።

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 26፤2016 – ፍቅረኛውን የገደለው ደቡብ አፍሪካዊው አትሌት ኦስካር ፒስቶሪየስ በይቅርታ ከእስር ተለቀቀ

ፓራሊምፒያን የሆነው ኦስካር ፒስቶሪየስ ፍቅረኛውን ሬቫ ስቴንካምፕን ከገደለ ከ11 ዓመታት ገደማ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝበት ማረሚያ ቤት በይቅርታ በነፃ ተለቋል።

ባለሥልጣናቱ ፒስቶሪየስ ከተፈረደበት ከ13 ዓመታት በላይ የእስር ጊዜውን ውስጥ ግማሹን በማጠናቀቁ ዛሬ ጠዋት መኖሪያ ቤቱ እንደገባ አረጋግጠዋል። የሟቿ ስቴንካምፕ እናት የቀድሞዋን አትሌት ከእስር የመለቀቅ ውሳኔ መቀበሏን ተናግራለች ነገር ግን ቤተሰቦችን በልጃችን ሞት የእድሜ ልክ እስራት ውስጥ ይገኛል ስትል አክላለች። ፒስቶሪየስ እ.ኤ.አ. በ2013 በቫላንታይን ወይም በፍቅረኛሞች ቀን በዋና ከተማው ፕሪቶሪያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመታጠቢያ ቤት በር ላይ አራት ጊዜ በመተኮስ ፍቅረኛዉን ስቴንካምፕን መግደሉ ይታወሳል፡፡

የ29 ዓመቷ ወ/ሮ ስቴንካምፕ የህግ ተመራቂ እና የተሳካላት ሞዴል ነበረች። በቲቪ አቅራቢነት የሰራች ሲሆን ትሮፒካ አይስላንድ ኦፍ ትሬዠር በተሰኘው የቲቪ ፕሮግራም ላይ ስትሳተግ ነበር። በህግ ከተመረቀች በኋላ በደል የተፈፀመባቸውን ሴቶች የሚረዳ የህግ ድርጅት ለመክፈት አቅዳ ነበር።ከፒስቶሪየስ ጋር የነበራት ግንኙነት ለሶስት ወራት ያህል ብቻ ነበር።

አሁን ላይ 37 አመቱ ላይ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2017 የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በስቲንካምፕ ግድያ 13 አመት ከአምስት ወር እስራት ተፈርዶበታል ፣ይህም ከዚህ ቀደም የተጣለበትን ተጨማሪ የስድስት አመት ቅጣት ነበር፡፡ፒስቶሪየስ ወንጀሉን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል ።ፒስቶሪየስ በቤቱ ውስጥ ሰርጎ የገባ ወንበዴ እንዳለ በማሰብ እንዲሁም ፍቅረኛው ስቴንካምፕ አልጋ ላይ ተኝታለች ብሎ መተኮሱን በፍርድ ችሎት ላይ ተናግሯል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ህግ መሰረት፣ ሁሉም ወንጀለኛ የጠቅላላ ቅጣቱን ግማሽ ያህል ከጨረሱ በኋላ ይቅርታ የማግኘት እድል ይኖረዋል፡፡ፒስቶሪየስ ገና የአንድ አመት እድሜ እንኳን ሳይሞላው በጤና እክል እግሮቹ ተቆርጠዋል። በመቀጠል በሰው ሰራሽ ህክምና ላይ ተመርኩዞ በአለም ታዋቂ አትሌት ለመሆን በቅቷል። በፓራሊምፒክ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል።

በለንደን 2012 ኦሎምፒክ ላይ አካል ጉዳተኛ ካልሆኑ አትሌቶች ጋር ተወዳድሯል። የሬቫ ስቴንካምፕ ግድያ እና ተከታዩ የወንጀል ሂደት በዓለም ዙሪያ ዋና ዜናዎች  ተቆጣጥሯል።

በበረከት ሞገስ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 26፤2016 – ሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ድንበር ደሴት የጦር መሳሪያ መተኮሷ ተሰማ

ሰሜን ኮሪያ ከ200 የሚበልጡ የጦር መሳሪያዎችን በምእራብ የባህር ዳርቻዋ ወደ ደቡብ ኮርያ ደሴት መተኮሷን የሴኡል ጦር አስታወቀ።ደቡብ ኮሪያ ጎረቤቷ ልምምድ ከማድረጓ በፊት ሰላማዊ ዜጎች በደሴቲቱ ላይ መጠለያ እንዲፈልጉ ትዕዛዝ አስተላልፋ ነበር፡፡

ደቡብ ኮርያ ድርጊቱን ጸብ ጫሪ ስትል አዉግዛለች፡፡እ.ኤ.አ. በ2010 የሰሜን ኮሪያ ጦር በዮኦፕዮንግ ደሴት ላይ በርካታ ጊዜ በመተኮሱ አራት ሰዎችን ገድሏል።ዛሬ የተተኮሰው የመድፍ ጥይቶች ወደ ደቡብ ኮሪያ ግዛት አልገቡም ሁሉም በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ልዩ ዞን ዉስጥ ወድቀዋል፡፡የደቡብ ኮሪያ የጋራ አዛዦች ክስተቱ “በህዝባችን እና በወታደራዊ ሃይላችን ላይ ምንም አይነት ጉዳት አላደረሰም” ቢሉም ድርጊቱ “በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ሰላምን አደጋ ላይ የሚጥል እና ውጥረትን የሚፈጥር ነው” ብለዋል።

ጥቃቱ የፒዮንግያንግ ወታደራዊ ትጥቅ እየገነባች ነው በማለት በባህረ ሰላጤው ላይ “በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ” ለሚችለው ጦርነት እየተዘጋጀች መሆኑን ማስጠንቀቂያ የሰጠችውን ተከትሎ ነው።በአቅራቢያው ባሉ ሁለት ደሴቶች ላይ ያሉ ባለስልጣናት ሲቪሎች መጠለያ እንዲፈልጉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ሺን ዎንሲክ በዛሬዉ እለት በሰጡት መግለጫ “ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ማለዳ ላይ የመድፍ ልምምዷን ማስቀጠሏ በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ሰላምን አደጋ ላይ የሚጥል እና ውጥረትን የሚፈጥር የቅስቀሳ ተግባር ነው” ብለዋል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 26፤2016 – በአራዳ ክፍለ ከተማ በተዘጋጀ የገና ባዛር ላይ የአገልግሎት ጊዜያቸው እና ምርታቸው አጠራጣሪ የሆኑ የምግብ ምርቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጀ የገና በጥራታቸው ላይ አጠራጣሪ የሆኑ የምግብ ምርቶች መያዛቸውን እና የናሙና ምርመራ እየተደረገ መሆኑን በአዲስ አበባ የምግብ እና መድሃኒት  ባለስልጣን የምግብ እና ጤና ነክ  ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር   አቶ ሚሬሳ ሚዴቅሳ በተለይም ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በአራዳ ክፍለከተማ በሚገኙ የበዓል የገበያ ቦታዎች ላይ ለምግብነት የቀረቡ የባልትና ምርቶች   የአገልግሎት ጊዜያቸው እና በውስጣቸው ስላለው ንጥረ ነገር መግለጫ ጽሁፍ የሌላቸው መሆኑም አጠራጣሪ እንዳደረጋቸው ተጠቁሟል።  

ምርቶቹ ምንም እንኳን የሀገር ውስጥ ቢሆኑም መቼ ፣የት እንደተመረተ ሊገልጽ የሚገባ  ነገር መኖር እንዳለበትም ዳይቴክተሩ  ተናግረዋል። በተጨማሪም  ናሙና ተወስዶ በምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር  ምርምራ እየተደረገባቸው ከሚገኙ ምርቶች መካከል  ሽሮ፣ በርበሬ እና ማር እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል።

በመሆኑም ለበዓል በተዘጋጁ  የገበያ ቦታዎች ላይ የአገልግሎት ምርት እና ይዘታቸው ያልተለጠፈባቸው ምርቶች  በተመለከተ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቀቄ እንዲያደርግ ተገልጿል ።

ወቅቱ በዓል በመሆኑ  በምግብ ነክ ምርቶች  ላይ  ተገቢውን ቁጥጥር  በልዩ መልክ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን በማንሳት   ህብረተሰብ  አጠራጣሪ ነገር ሲመለከት ጥቆማ  መስጠት እንዳለበት  አቶ ሚሬሳ ሚዴቅስ ጨምረዉ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 22፤2016 – የፓስፊክ ሀገር የሆነችው ኪሪባቲ 2024 ዓመትን በቀዳሚነት ተቀበለች

????ብራዚላውያን ነጭ ልብስን በመልበስ ወደ ባህር አበባ በመውሰድ አዲሱን ዓመት ተቀብለዋል

በብራዚል የአዲስ አመት ዋዜማ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ቀን ነው። አንዳንድ ብራዚላውያን አዲሱን ዓመት ለመቀበል በርካታ ወጎች ያሉባቸው ሲሆን ነጭ ልብስ ከመልበስ አንስቶ የተለያዩ ስነ ስርዓቶች ያካሄዳሉ። በሃይማኖታዊ በሆኑ እና ሃይማኖታዊ ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ ነጭ ልብሶችን የመልበስ ባህሉ ኢማንጃ የሚባል ሲሆን የዮሩባ አምላክ ወይም “የባህር ንግሥት” ተብሎ የሚጠራውን በሚያከብሩ አምላኪዎች ዘንድ በሰፊው ተቀባይነት አግኝቷል።

እንዲሁም ነጭ ልብስ ለብሰው ኢማንጃን የሚያመልኩ ሰዎች ያለፈውን ዓመት ምስጋና ለማቅረብ በዓመቱ መጨረሻ አበባዎችን ወደ ባሕሩ ይወስዳሉ። የአገሪቱን ከፍተኛ ተከታይ ያለውን የካቶሊክ እምነት ሲሆን አማኞቹን ጨምሮ ነጭ ልብስ ለብሰው ወደ ባህር በመውረድ በመጪው ዓመት ሰላምና ስምምነትን ለማሳየት የሚደረግ ነው ያሉትን ባህል አክብረዋል። ከነጭ ልብስ በተጨማሪ ቀጣዩ ዓመት የተለየ ለማድረግ የተለያዩ ቀለማት ያላቸውን ልብሶች መልበስም የተለመደ ነው።

ምንም እንኳን የልብስ ቀለም ምርጫ ግላዊ ቢሆንም ፣ እያንዳንዱ ቀለም ለመጪው ዓመት የሚወክለው ትርጉም ይኖራል። ነጭ ሰላምን ፣ስምምነትን እና መረጋጋትን ይጠቁማል። ወርቃማ ቀለም ያላቸው አልባሳት ደግሞ ብርሃንን እና ብልጽግናን ያመላክታል። ብራማ አልባሳት ወጣትነት ያሳያል።በመጪው ዓመት መነቃቃት እና ደስታን እየፈለጉ ከሆነ ቢጫ እንዲለብሱ ይመከራል።

ሰማያዊ ለመተማመን እና ለመረጋጋት ፣ አረንጓዴ ለዕድገት፣ ራስን ለማደስ እንዲሁም ለተስፋ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ቡናማ ለጠንካራነት እና ደህንነት እንፈልጋለሁ የሚለውን ያሳያል።ንጥቁር ውበት እና ኃይልን ይጠቁማል። ቀይ ላሳካ የምፈልገው ህልም አለኝ እንዲሁም ፍቅርን የተራብኩኝ ነው የሚለውን አካቶ ይዟል።

በሌላ በኩል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአዲሱን አመት መምጣት የሚያሳዩ የርችት ስራዎችን ለመመልከት የለንደን እና የኤድንበርግ ጎዳናዎችን ሞልተው ሌሊቱን አሳልፈዋል። በመላው አውሮጳ በሚገኙ ከተሞች ሰዎች የ2024 መባቻን ለማክበር በታዋቂ የከተሞቹ ምልክቶች ላይ ተሰብስበው አምሽተዋል። አፍሪካ በተመሳሳይ 2023 ዓመትን ተሰናብታለች።

አውስትራሊያን፣ ኒውዚላንድን እና በመላው እስያ የሚገኙ ሀገራትን ከሌላው የዓለም ክፍል አዲሱን ዓመት  ቀድመው የተቀበሉ ሲሆን የኪሪባቲ የፓሲፊክ ሀገር ነዋሪዎች ግን ከሁሉም ሀገራት ደግሞ ቀዳሚ ነበሩ። እንደበፊቱ ሁሉ፣ በሆንግ ኮንግ፣ ሲድኒ እና ዱባይ አስደናቂ የዓዲስ ዓመት ዋዜማ ትርኢቶች ተደርገዋል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 17፤2016 – በአርሲ ነገሌ ከተማ የባለቤቷን ሀብት ለመዉረስ በማሰብ ከወንድሟና ከወንድሟ ሚስት ጋር በመሆን በባሏ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ

በአርሲ ዞን አርሲ ነገሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የ45 ዓመቱ ከተማ አበበ የተባሉ ግለሰብ በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ናቸዉ ።

አቶ ከተማ ከዚህ በፊት በትዳር ህይወት የነበሩ ቢሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች የትዳር ግንኙነታቸው ሳይሳካ ቀርቶ በፍች ይደመደሜ።

ለብቻቸዉ ለተወሰነ ጊዚያት እየኖሩ እያሉ በአጋጣሚ ትግስት ደረጀ የተባለች የአርሲ ነገሌ ከተማ ነዋሪ ጋር ይተዋወቁና በትዳር ይጣመራሉ። ከተማ አበበ ከትግስት ደረጀ አብረዉ እየኖሩ እያለ አቶ ከተማ  በሸቀጣሸቀጥ ንግድ የተዋጣላቸዉ ሰዉ ይሆናሉ።

ረዳት ሰራተኛ መቅጠር አለብኝ ብለው ሰው ሲፈልጉ ባለቤታቸው ትግስት ሌላ ሰዉ ከሚቀጠር ወንድሜ ስራዉን ቢያግዝ ብላ ትጠይቃለች ።ከተማ በአንድ በኩል በሁለት ጥንዶችና ባለትዳሮች መካከል ቤተሰብ ጣልቃ ማስገባት ጥሩ እንዳልሆነ ቢረዱም ለባለቤታቸው ትግስት ካለቸው ፍቅር የተነሳ ይስማማሉ።

የትግስት ወንድም ሙሉቀን ደረጀ ወደ ከተማ ቤት ይመጣና ስራ ይጀምራል። ሙሉቀን ደረጀ ነገሌ አርሲ ከተማ ነዋሪ ከሆነችዉ ሰላም ፋንታሁን ከተባለች ልጅ ጋር ፍቅር  ይጀምራል።

ከተማ አበበ የባለቤቱ ወንድም ሙሉቀን  ፍቅር መጀመር ተገቢ መሆኑን ቢረዳም ከልጅቷ ጋር ከተዋወቀ ጊዜ አንስቶ ስራ እየሰራ እንዳልሆነ  ለባለቤቱ ትግስትና ወንድሟን ሙልቀንን  ይነግራቸዋል።በዚህም ምክምያት ከተማ አበበና የባለቤቱ ወንድም ሙሉቀን ጋር ቅራኔ ይፈጠርና ከቤት ይወጣል።

የባለቤቱ ወንድም ከቤት ከወጣ ጀምሮ ቂም በመያዝ ከተማን አበበ ለመግደል ያስባል።የእቅድ ተባባሪ እንድትሆን እህቱን ትግስትን ያማክርታል ።ግለሰቡን ከገደሉት በኋላ ንብረቱን አብረዉ እንደሚውርስ ያሳምናታል።

የካቲት 10 ቀን 2015 ከምሽቱ 6:00 ትግስት ደረጀ፣ ሙሉቀን ደረጀ እና የሙሉቀን ፍቅረኛ ሰላም ፋንታሁን ፣ከተማ አበበን በተኛበት በመጥረቢያ ቆራርጠዉ ከገደሉት በኋላ ቤት ዉስጥ ይቀብሩታል ።

ድርጊቱን ከፈፀሙ በኋላ ከተማ አበበ ቤት እንዳልመጣ ለፖሊስ ያመለክታሉ።ፖሊስ የአቶ ከተማ አበበ መጥፋት ከደረሰዉ በኋላ ክትትል ሲጀምር ሙሉቀን ወደ አዲስ አበባ መሄዱን ሲሰማ በመጠራጠር እህቱንና ፍቅረኛዉን በቁጥጥር ስር ያዉላቸዋል።

ትግስት በቁጥጥር ስር  ዉላ ምርመራ ሲደርግባት ወንድሟ ድርጊቱን  እንዳቀነባበረዉ ትናገራለች።ፖሊስም ባለቤቱንና የሙልቀን ፍቅረኛ ሰላም ፋንታሁንን በቁጥጥር  ስር አውሎ ሙሉቀንን ሲፈልግ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ  ክፍለ ከተማ በቁጥጥር ስር ያዉላቸዋል።

ፖሊስና አቃቢ ህግ  በጋራ በመሆን ምርመራ መዝገቡን በማጣራት ክስ ይመሰርታል።የምዕራብ አርሲ ዞን  ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሀብት ያላግባብ ለመዉረስ በፈፀሙት ድርጊት እያንዳንዳቸዉ ላይ የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንደወሰነባቸዉ የምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ከድር ችቦ በተለይ ለብስራት ቲቪና ራዲዮ ገልፀዋል።

በበቀለ ጌታሁን