መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 – በቻይና የሰው መልክ ያላት የሮቦት የመስተንግዶ ሰራተኛ ከፍተኛ ትኩረት ስባለች

በቻይና ቾንግኪንግ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ሬስቶራንት ውስጥ የምትሰራ የአንድሮይድ አስተናጋጅ የደንበኞችን ትኩረት እየማረከች ሲሆን የሮቦቲክ እንቅስቃሴዎች አስገራሚ መሆኑ ተነግሯል።

በዓለማችን ላይ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኤኤል የሚንቀሳቀሱ ሮቦቶች የሰውን ስራ ሊቀሙ ይችላሉ የሚለው ስጋት በስፋት እየተደመጠ ይገኛል። ይህንኑ የሚያጠናክር ክስተት በቻይና ሬስቶራንት ውስጥ በአስተናጋጅነት የምትሰራ ሮቦት የመስተንግዶ ሰራተኛ መነጋጋሪ የሆነች ሲሆን ስራችንን እንቀማለን ያሉ ዜጎች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሟታል።

ሰው መሳይ ገጽታ ያላች ይህው የመስተንግዶ ሰራተኛ ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታን ያዳበረች ሲሆን ወደ ቾንግቺንግ ምግብ ቤት ሰዎች ሲገቡ ሰላምታ መስጠትን ጨምሮ ትእዛዛቸውን መቀበል ትሰራላች። በተጨማሪም ያዘዙትን ምግብ ወደ ገበታዎቻቸው ታቀርባለች።አንዳንድ ተጠቃሚዎች የአንድሮይድ አስተናጋጇ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ ህይወት ያላት እንደምትመስል ገልፀዋል።

የቾንግኪንግ ሮቦቲክ አስተናጋጅ ቪዲዮ ከተጋራ በኃላ  አስተናጋጇ ሰው መስላቸው ግራ የተጋቡ ሰዎች መኖራቸው ተገልጿል።የአንድሮይድ አስተናጋጇ ስራ ፈጣሪ የ26 አመት ሴት መሆኗ ተነግሯል።

አስተናጋጇ ሮቦት ሜካፕ የምትጠቀም የስራ አፈፃፀሟ ሰው ናት ብለው በርካቶች እንዲጠራጠሩ መደረጉ ደንበኞችን ለመሳብ እንደረዳት ስራ ፈጣሪዋ ወይዘሮ ኪን ገልጻለች።ሰዎች ወደ ኪን ሬስቶራንት የሚመጡት ለጣፋጩ ምግቦች እና መጠጦች ብቻ ሳይሆን የአንድሮይድ የመስተንግዶ ሰራተኛዋን ነመመልከት ጭምር ሆኗና።

በቻይና በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ፈጠራው ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 – በአዲስ አበባ ከተማ ለሴፍቲ ታንከር አገልግሎት በተዘጋጀ ያለተከደነ ታንከር ዉስጥ ለውሃ ዋና የገባው የ16 ዓመት ታዳጊ ህይወቱ አለፈ

???? ግንብ ተደርምሶ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ አራት በጎች ሞተዋል

በአዲስ አበባ ከተማ ህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አደይ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ግቢ ዉስጥ ለሴፍቲ ታንከር አገልግሎት የተዘጋጀና ያለተከደነ ታንከር ዉስጥ የ16 ዓመት ታዳጊ ውሃ ዋና ለመዋኘት ገብቶ ህይወቱ ማለፉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ጠላቂ ዋናተኞች አስከሬኑን አዉጥተዉ ለፖሊስ ማስረከባቸውን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ሰኞ ህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 6:30 ሰዓት ላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 6 ሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን ጀርባ ግንብ ተደርምሶ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ አራት በጎች መሞታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል

በአዲስ አበባ ከተማ በእርጅናና በግንባታ ጥራት ምክንያት በመደርመስ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ በመሆኑ አስፈላጊዉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ ንጋቱ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2015 ዓ.ም ክረምት ወር በጉለሌ ክፍለ- ከተማ ቀጨኔ መካነ-መቃብር ግንብ ተደርምሶ የሁለት ሰዎች ህይወት እንዲሁም 112 በጎች ህይወታቸዉ ማለፉ ይታወሳል።

በትግስት ላቀው

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 – በኢትዮጲያ በየዓመቱ ከ5ሺ በላይ እናቶች በማህፀን ካንሰር ህይወታቸው ያልፋል ተባለ

በኢትዮጲያ በየዓመቱ ከ7 ሺ 4 መቶ 45 በላይ አዳዲስ ታማሚዎች በሁማን ፓፒሎማ ቫይረስእንደሚያዙ እና ከ5 ሺ 3 መቶ በላይ እናቶች ደግሞ  ህይወታቸውን እንደሚያጡ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ህፃናት እና አፍላ ወጣቶች መሪ ስራ አስፈፃሚ እና የክትባት አገልግሎት ዴስክ አማካሪ አቶ መንግስቱ ቦጋለ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት የማህፀን በር ካንሰር ሁማን ፓፒሎማ ቫይረስ/HPV/ በተሰኘ በዓይን በማይታይ ተህዋስ አማካኝነት  እንደሚከሰት ገልፀዋል።

በሽታው በማህፀን ጫፍ ላይ ያልተለመደ የህዋስ ስርጭት ሲከሰትና በመላው የማህፀን ጫፍ አካባቢ ሲዛመት የሚፈጠር ህመም ነው ብለዋል። በተጨማሪም ከዚህ የአካል ክፍል የሚነሳና በአካባቢው ያሉትን የአካል ክፍሎች ድረስ ሊሰራጭ የሚችል የካንሰር አይነት እንደሆነም ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።

በቅርቡ በወጣው የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት  በአለም አቀፍ ደረጃ በካንሰር አማካኝነት ለሚከሰቱት ሞቶች የማህጸን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር በመቀጠል ሁለተኛውን ደረጃ እንደያዘ አመላክቷል፡፡

በምህረት ታደሰ

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 –በጋዛ ሰርጥ ባለፉት 48 ስዓት ከ800 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል

እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገው ጦርነት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ ሞት እና ውድመት ተመዝግቧል። ባለፉት 48 ሰዓታት ቢያንስ 800 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። ጦርነቱ ከጀመረበት ከጥቅምት 7 አንስቶ በየቀኑ ከሚመዘገበው ሞት ከፍተኛ እንደሆነ ተመላክቷል።

ከሰሜን እስከ ደቡብ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ምንም አይነት ደህንነት የለንም ሲሉ ተናግረዋል። የእስራኤል ጦር በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ ላይ ለሁለተኛ ቀን ኢላማ በማድረግ ጥቃት ፈፅሟል። በርካታ ቤቶች ወድመዋል፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪ ከፍርስራሹ በታች ሰዎች ተቀብረዋል። እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ውስጥ በካን ዮኒስ የተወሰኑ ሰፈሮች የሚኖሩ ነዋሪዎችን ለቀው እንዲወጡ ጠይቃለች።

ወደ ሌሎች የከተማው ክፍሎች ወይም ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሚወስዱ መንገዶች ወድመዋል። ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጋዛ ከ15,500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። በሌላ በኩል በሊባኖስ የሚገኘው ሃማስ ለወጣት ፍልስጤማውያን የጥቅምት 7 ጥቃቶችን በማጣቀስ “የአል-አቅሳ ጎርፍን” እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል።

በመግለጫው በጥቃቱ የተገኘው ውጤት እንዲቀጥል እና ለፍልስጤም ህዝብ ድል እንዲቀዳጅ ጥሪው አቅርቧል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 –በአዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ በደረሱ ድንገተኛ አደጋዎች የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናቶች በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት የእሳት አደጋዎች ንብረት ሲወድም አንድ ሰው ድልድይ ስር ህይወቱ አልፎ መገኘቱን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የመጀመሪየው አደጋ ያጋጠመው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ጎሮ ጉሊት አካባቢ በተነሳ የእሳት አደጋ ንብረትንቱ የአንድ ግለሰብ የሆነ 15 ክፍል ቤቶች መቃጠላቸውን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

የእሳት አደጋዉ ተስፋፎቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን ቤቶቹ የተገነቡበት ግብዓት በቀላሉ መቀጣጠል የሚችሉ በመሆኑ ቃጠሎዉ ሊስፋፋ ችሏል ተብላል።በሌላ በኩል ቅዳሜ 10:30 ሰዓት ላይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ብርጭቆ ፋብሪካ ላይ ባጋጠመ የእሳት አደጋ በፋብሪካዉ ማሽነሪ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሳል።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር ስድስት የእሳት አደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ ከ42 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር የተሰማሩ ሲሆን የእሳት አደጋዉ ወደሌሎች የፋብሪካዉ ክፍሎች ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን በሰዉ ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም።

እሁድ ህዳር 23 በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ራስ መኮንን ድልድይ ስር በሚገኝ ወንዝ ዕድሜዉ 30 ዓመት የተገመተ ሰዉ ህይወቱ አልፎ መገኘቱን አቶ ንጋቱ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቲቪ ተናግረዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አስከሬን አዉጥተዉ ለፖሊስ አስረክበዋል።የግለሰቡ አሟሟት ፖሊስ እያጣራ ይገኛል።

በትግስት ላቀው

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 –በቫይታሚን ያልበለፀጉ የስንዴና ዘይት ምርቶች ወደ ሃገር ዉስጥ እንዳይገቡ ቢታገዱም በገበያ ላይ እንዳሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዛሬዉ እለት ባወጣዉ ማሳሰቢያ ከ ሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቫይታሚን ያልበለጸጉ የስንዴና የምግብ ዘይት ምርቶች ወደ ሀገርቤት እንዳይገቡ ቢወሰንም በገበያ ላይ እንደሚገኙ አስታዉቋል።

በአንዳንድ አስመጪዎች አማካኝነት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት ምርቶች በተቀመጠው የፎርትፊኬሽን አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ መሰረት በቫይታሚን ሳይበለጽጉ ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ነዉ ያለዉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፤ ምርቶቹ በብዛት በፍራንኮ ቫሉታ የሚገቡ ስለሆነ ስለ አስገዳጅ ደረጃው በአስመጪዎች በኩል መረጃው በበቂ ሁኔታ ባለመድረሱ ነዉ ሲልም ምክንያት ያለዉን በማሳሰቢያዉ ጠቅሷል።

ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከሚኒስቴሩ ካገኘዉ መረጃ እንደተመለከተው ፤በዚህ ምክኒያት ምርቶቹን በቫይታሚን መበልጸግ በኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃ ቢወጣላቸዉም በተቃራኒው ምርቶቹ ተግባራዊ ሳይደረጉ ወደ ሀገር ዉስጥ መግባታቸውን ሚኒስቴሩ አረጋግጧል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በማሳሰቢያዉ ፤ ከህዳር 24 ጀምሮ የምርቶቹ አስመጪ ነጋዴዎች በቫይታሚን ያልበለፀጉ ዘይትና የስንዴ ዱቄት ወደ ሀገር ዉስጥ ማስገባት እንደማይችሉ አስታዉቋል። ሚኒስቴሩ ይህንኑ ተላልፈዉ በሚገኙት ላይም  እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 –በደቡብ አፍሪካ በተነሳ ብጥብጥ 7 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ መቃጠላቸዉ ተሰማ

በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ረብሻና ብጥብጥ በምታስተናግደዉ ጆሃንስበርግ ከተማ ከትናንት በስቲያ ተከስቶ ነበር በተባለ ረብሻ 7 ሰዎች ግድያ ከተፈጸመባቸዉ በኋላ አስክሬናቸው ተቃጥሎ መገኘቱ ተሰምቷል።

ተከስቶ በነበረዉ ሁከት በቅድሚያ የሁለት ሰዎች አስክሬን ከተገኘ ከሰዓታት በኋላ የተቀሩት ሰዎችም በተመሳሳይ መንገድ ተገድለዉ መገኘታቸውን የፖሊስ ቃልአቀባይ ለ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ተናግረዋል። ሁሉም የተገደሉት ሰዎች በ 20ዎቹ የእድሜ መጀመሪያ የሚገኙ ናቸዉ ተብሏል።

ሁሉም ወጣቶች የመንጋ ጥቃት በሚመስል ተሳድደዉ ፣ ታስረዉና በስተመጨረሻም ተቃጥለዉ መገደላቸዉን ፖሊስ ገልጿል። ግድያዉ በምን አነሳሽነት መፈጸሙን ፖሊስ እንዳላወቀ የጠቀሰ ሲሆን ግድያዉንም ማህበረሰቡ አዉግዟል።

ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ 2023 ሩብ አመት ብቻ በየእለቱ 68 ሰዎች የሚገደሉባት መሆኑን እና ይህም እ.ኤ.አ በ 2019 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከነበረው ሲነጻጸር የ 20 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ በዘገባዉ ተጠቅሷል።

በበረከት ሞገስ

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 –በቡታጅራ ከተማ ከ20 ሺህ በላይ ሀሰተኛ የብር ኖት ሲያዝ ተጠርጣሪው ለጊዜው ማምለጡ ተነገረ

በቡታጅራ ከተማ 03 ቀበሌ ልዩ ስሙ አባይነህ አዳማ ሰፈር አንድ ሱቅ ገብቶ የ15 ብር የሞባይል ካርድ ገዝቶ ባለ 200 ብር በመስጠት 180 ብር መልስ ለመቀበል በመጠባቅ ላይ እያለ የብር ኖቱ የተጠራጠሩት የሱቅ ነጋዴ አካባቢው ላሉ ወጣቶች ሁኔታውን ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ጊ እንደታወቀበት የገባው ግለሰብ በፌስታል የያዘው 22 ሺህ 200 ሀሰተኛ ብር ጥሎ ከአካባቢው በመሮጥ ያመልጣል።

በአካባቢው የነበሩ ወጣቶች ግለሰቡ ጥሎት የሄደውን 22 ሺህ 200 ብር በመያዝ ለቡታጅራ ከተማ ፖሊስ በማስረከብ ጥቆማውን ማድረሳቸው የቡታጅራ ከተማ የመንግስት ኮሙኒኬሽን የሚዲያ ዘርፍ ቡድን መሪ ሀሰን ሁሴን ለብስራት ራዲዮና ቴሌቬዥን ገልፀዋል።

በከተማዋ ሌሎችም ሀሰተኛ የብር ኖት ተሰራጭቶ ሊሆን ስለሚችል ህብረተሰቡ ማንኛውም ግብይት ሲፈፅም ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባና ማንኛውም አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ካሉ ለከተማው ፖሊስ ጽ/ቤት ጥቆማ እንዲያደርግ የቡታጅራ ከተማ የመንግስት ኮሚንኬሽን የሚዲያ ዘርፍ ቡድን መሪ ሀሰን ሁሴን ለብስራት ራዲዮና ቴሌቬዥን ተናግረዋል።

በበቀለ ጌታሁን

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 –በአዲስ አበባ የግል የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ አደደሉም ተባለ

???????? አንዳንድ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ ዳተኛነት ይታይባቸዋል

በትናንትናው እለት የተከበረዉን አለማቀፉን የአካል ጉዳተኞችን ቀን በማስመልከት የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፤ የአካል ጉዳተኞችን አዋጅ የማዉጣት ሂደት መጓተቱን ተከትሎ እንዳሳሰበዉ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን በላከዉ መግለጫ አስታዉቋል።

የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ጥላሁን ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አካል ጉዳተኞች እየደረሰባቸዉ ያለዉ መሰረታዊ የመብት ጥሰት መጨመሩን ተናግረዋል። በማብራሪያቸዉ በአዲስአበባ ያሉ የግል የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለመቀበል ፈቃደኝነቱ እንደሌላቸዉ ተናግረዋል። በተመሳሳይ አንዳንድ የግል ት/ት ቤቶችም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለመቀበል ዳተኛነት እንደሚያሳዩ አቶ ሙሴ አንስተዋል።

“የት/ት ተቋማቱ ሀይ ባይ አጥተዋል” ያሉት የማህበሩ ዳይሬክተር ፤ ይህን መሰል አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰዉን የመብት ጥሰት የሚከላከል የአካል ጉዳተኞች አዋጅ አመለመጽደቁ ያመጣዉ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተዋል። በተመሳሳይ አካል ጉዳተኞች መዋቅራዊ በሆነ መልኩ በቅጥር ሂደት ላይ አድልዎ እንደሚፈጸምባቸዉም ተናግረዋል። አካል ጉዳተኞቹ ቅጥር ካገኙ እንኳን ህጋዊ መብታቸውን እንዳያገኙ በቀጣሪዎች በርካታ የመብት ጥያቄ ያነሳሉ በሚል በርካታ ፈተናዎችን እንደሚጋፈጡም አቶ ሙሴ ጠቁመዋል።

ማህበሩ በአካል ጉዳተኞች አዋጅ አለመጽደቅን ተከትሎ ባወጣዉ መግለጫ  የኢፌድሪ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ፤ የአዋጁን መዉጣት አስፈላጊነት ለካቢኔያቸዉ ማህበሩ ማስረዳት የሚችልበትን መድረክ እንዲያመቻቹም ጠይቋል።

በበረከት ሞገስ

መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 24፤2016 –በቱርክ የጥርስ ሀኪም ነኝ በማለት የፅዳት ሰራተኛው የታካሚውን አራት የፊት ጥርሶች በማውለቁ በእስራት ተቀጣ

በኢስታንቡል የፍትሐ ብሔር ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ እንዳመላከተው የ42 ዓመቱ ሃካን ኢልዲሪም የኢስታንቡል ነዋሪ ሲሆን በከባድ የጥርስ ሕመም መሰቃየቱን ተከትሎ በካጊታን አውራጃ ወደሚገኘው የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ደውሎ አስቸኳይ የህክምና ቀጠሮ ይይዛል። የታካሚውን ቀጠሮ የተቀበለው ሴማል ሴናስላን የተባለው ግለሰብ እራሱን እንዳ ጥርስ ሀኪም በማስተዋወቅ ሀካንን በምሽት ክሊኒኩ መጥቶ የጥርስ ችግሩ እንዲመረመር እና እንዲፈታ ይነገረዋል።

ታካሚው በእለቱ ወደ ክሊኒኩ ሲመጣ፣ ዪልዲሪም የበለጠ ምቾት እንዲሰማው ለማድረግ በጥርስ ሕክምና ዩኒቨርሲቲ መምህር ነኝ ብሎ ይነግረዋል። የታካሚውን ጥርስ ለአጭር ጊዜ ከመረመረ በኋላ ሴማል ሼናስላን አራት የፊት ጥርሶቹ መነቀል እንዳለባቸው ይነግረዋል። በሁኔታው የተደናገጠው ይልዲሪም እንዴት ይህ ይሆናል ሲል ሀሰተኛው የጥርስ ሀኪም መልሶ ስራዬን እያስተማርከኝ ነው? ሲል ይበሳጫል።ሰውዬው በጥርስ ሕክምና ዩኒቨርሲቲ መምህር ነኝ ብሎ ሲፎክር ከሰማ በኋላ ሃካን ኢልዲሪም ሌላ ምንም ተጨማሪ ነገር ሳይናገር መታከሙን ይቀጥላል።

ሴማል ሼናስላን የ42 ዓመቱን ሰው በማደንዘዝ አራት የፊት ጥርሶቹን ነቅሎ ማውጣቱ አስፈላጊ መሆኑን አጥብቆ በመናገር በጣም በሚያምር ሰው ሰራሽ ጥርስ እንደሚተካለት ይነግረዋል። ይልዲሪም ‘የጥርስ ሀኪሙ’ የጠየቀውን 1,000 የቱርክ ሊራ ወይም 35 ዶላር ክፍያ ፈፅሟል። ከህክምናው በኃላ በሼናስላን የፊርማ ማዘዣ ወደ ፋርማሲ ይሄዳል። ሃካን ኢልዲሪም በመጀመሪያ ፋርማሲስቱ ለመድኃኒት ማዘዣ ሊያስከፍለው ሲሞክር ሼናስላን በማመን ከባድ ስህተት እንደሠራ መጠራጠር ይጀምራል።ይህ ከፋርማሲስቱ ጋር ያስማማዋል።

በማግስቱ ከባድ የጥርስ ህመም ተሰምቶት ወደ ክሊኒኩ ሲያመራ ያከመው ግለሰብ እንዳለው የጥርስ ሀኪም ሳይሆን የፅዳት ሰራተኛ መሆኑ ይደርስበታል።ህመሙን መቋቋም ባለመቻሉ ሃካን ኢልዲሪም በመጨረሻ ወደ ድንገተኛ ክፍል እንደገባ የፍርድ ቤት ሰነዶች ያሳያሉ። በፊቱ እና ከዓይኑ ስር እብጠቶች የነበሩበት ሲሆን ከህመሙ ለመዳን አንድ ወር ያህል መታገስ ነበረበት።

በስተመጨረሻ ሀሰተኛው ዶክተር በፈፀመው ድርጊት የኢስታንቡል የፍትሐ ብሔር ፍርድ ቤት ጥፋተኛ በማለት በሁለት ዓመት ከስድስት ወራት እስር እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል።

በስምኦን ደረጄ