ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 17፣ 2012-በድሬዳዋ ከተማ በትናንትናው ዕለት የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የአራት ሰዎች ህይዎት ማለፉን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

በድሬዳዋ ከተማ በትናንትናው ዕለት የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የአራት ሰዎች ህይዎት ማለፉን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ዝናቡ ትናንት ከቀኑ 7 ሰአት ከ30 ጀምሮ የጣለ ሲሆን፥ ያስከተለው ጎርፍ የመኖሪያ ቤቶችን ማፈራረሱንም ፖሊስ አስታውቋል።

በጎርፉ ሳቢያ በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩ የ4 አመት ህጻን እና የ2 ወር ጨቅላ ህይወታቸው አልፏል ነው ያለው።

እንዲሁም በሌላ መኖሪያ ቤት የነበሩ የ19 አመት ታዳጊ እና የ45 አመት ጎልማሳ በጎርፍ ተወስደው ህይወታቸው አልፏል።

ከዚህ ባለፈም በሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በጎርፉ ሳቢያ ከ31 በላይ ቤቶች ሲፈርሱ በርካታ ቤቶችም በጎርፍ ተጥለቅልቀው ንብረቶች ወድመዋል። በጎርፍ የተወሰዱ 3 የባጃጅና የፎርስ ተሽከርካሪዎችም አሸዋ ውስጥ ተቀብረው መገኘታቸውንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 17፣ 2012-ታግተው የነበሩ አምስት ኢትዮጵያውያንን ከእገታ ተለቀቁ

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሪያድ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ደዋድሚ ከተማ ውስጥ በአንድ ቤት ውስጥ አምስት ኢትዮጵያውያን ታግተው እንደነበር በፌስ ቡክ ገጹ አስታወቋል። ከታጋቾቹ ውስጥ አንዱ ወንድ ሲሆን አራቱ ሴቶች መሆናቸውንም ገልጿል።

አጋቾቹ ወደ ታጋች ቤተሰቦች በማስደወል በነፍስ ወከፍ 10 ሺህ የሳዑዲ ሪያል እንዲከፍሉ እና ከዚያ በኋላ እንደሚለቋቸው አሳውቀዋቸዋልም ነው ያለው።

ይህን የማያደርጉ ከሆነም ቅጣቱ ሞት ነው በማለት እንደዛቱባቸው ከታጋች ቤተሰቦች ማወቅ መቻሉን ጠቅሷል።

የተጠየቁትን ገንዘብ የመክፈል አቅም ያልነበራቸው ዜጎችም በአንድ ቤት ተዘግቶባቸው ለብዙ ጊዜያት እንደቆዩም ነው የገለጸው።

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 17፣ 2012-መንትያ እህትማማቾቹ በኮሮና ቫይረስ ህወታቸዉ አለፈ

ኬቲ እና ኤማ ዴቪስ የተባሉት መንትያ አህትማማች በሶስት ቀናት ልዩነት ዉስጥ በኮሮና ቫይረስ ህይወታችዉን አጥተዋል፡፡

ባሳለፍነዉ አርብ በሳዉዝአፕተን ጠቅላላ ሆስፒታል የ37 ዓመት እድሜ ያላት ኤማ ህይወቷ ያለፈ ሲሆን ባሳለፍነዉ ማክሰኛ ደግሞ ኬቲ ህይወቷን አጥታለች፡፡

ሌላኛዋ እህታቸዉ ዞኢ ስለዚሁ ሁኔታ ተጠይቃ ስትናገር ሁሌም አብረን ወደዚህች ምድር መጥተናል አብረን እንሄዳለን ሲሉ ይናገሩ ነበረ ብላለች፡፡

ኬቲ በህጻናት ሆስፒታል ዉስጥ በነርስነት ሙያ ትሰራ የነበረ ሲሆን ኤማ በቀድሞ ሙያዋ ነርስ ነበረች፡፡

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 16፣2012-የቤት ሰራተኛዉን ለመሸጥ ማስታወቂያ በፌስቡክ ያወጣዉ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

ነዋሪነቱ በሊባኖስ የሆነዉና የሶርያ ዜግነት ያለዉ አሰሪ የናይጄሪያ ዜግነት ያላትን የቤት ሰራተኛዉን ለመሸጥ በፌስቡክ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡የ30 ዓመት እድሜ ያላት ግለሰቧ በ1ሺ የአሜሪካ ዶላር ለሽያጭ ቀርባለች፡፡

ድርጊቱ በማህበራዊ ገጽ ትስስር ሲዘዋወር የተመለከተዉ በሊባኖስ የናይጄሪያ ኤምባሲ ጉዳዩን ለሊባኖስ መንግስት ያሳዉቃል፡፡ድርጊቱን የፈጸመዉ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዉሏል፡፡

በኩዌት በጥቁር ገበያ በማህበራዊ ገጽ ትስስር አማካኝነት የቤት ሰራተኞችን እንደሚሸጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 16፣2012-ከህክምና ማዕከል ያመለጠዉ የኢቦላ ታማሚ እየተፈለገ ይገኛል

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለፈዉ ሳምንት ከጤና ማዕከል ያመለጠዉ ሰዉ እየተፈለገ ይገኛል፡፡የጤና ባለሙያዎች ማህበረሰቡ ግለሰቡን እንዳይሸሽጉ እየመከሩ ይገኛል፡፡

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከኢቦላ ነጻ መሆኑን ላታዉጅ ቀናት ሲቀሯት 6 ሰዎች በኢቦላ መያዛቸዉ ተረጋግጧል፡፡በ2018 ዓመት የተቀሰቀሰዉ ኢቦላ ከ2200 በላይ ሰዎችን ህይወት መንጠቁ ይታወሳል፡፡

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 16፣2012-ግብጽ የረመዳንን ወቅት ምክንያት በማድረግ በአንዳንድ ክልከላዎች ላይ ማሻሻያ አደረገች

በዚህም መሰረት በግብጽ የሚገኙ የንግድ ተቋማት እንደሚከፈቱ የተነገረ ሲሆን ምግብ ቤቶች የምግብ አቅርቦትን እንዲሰጡ ተፈቅዷል፡፡በመስጊድ ዉስጥ የሚደረገዉ የጸሎት ስነስርዓት ግን በክልከላዉ ቀጥሏል፡፡

በግብጽ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ የ287 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 3,891 ደግሞ በቫይረሱ ተጥቅተዋል፡፡

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 15፣2012-አጫጭር መረጃዎች

~ በምስራቃዊ ጀርመን የሚገኘዉ የቮልስ ዋገን የመኪና አምራች ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ፡፡ ለአምስት ሳምንታት ስራዉን አቁሞ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የኤሌትሪክ ተሸከርካሪዎችን ማምረት መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ በኮሮና ምክንያት በጀርመን ስራዉን አቁሞ የነበረዉ መርሴዲስ ቤንዝ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚመለስ አስታዉቋል፡፡

~ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በእስራኤልና በግብጽ መካከል ለምትገኘዉ የጋዛ ሰርጥ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ተቋሙ ለጋዛ ሆስፒታል የጽኑ ህሙማን መከታተያ ክፍል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለግሷል፡፡

~ ኢንዶኔዥያ እስከ ወርሃ ሰኔ መጀመሪያ ድረስ በባህርና በአየር በሀገር ዉስጥ የሚደረግ ጉዞን ከለከለች፡፡ በህዝብ ብዛቷ በአለም አራተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘዉ ኢንዶኔዥያ የ647 ሰዎች ህይወት በቫይረሱ የተነሳ አልፏል፡፡

~ የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኮሮና ቫይረስ የተነሳ ያጋጠመዉን የገቢ እጥረት ተከትሎ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡ በዚህ በ44 የሀገሪቱ ክለብ ዉስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

~ በናይጄሪያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከአንድ ግዛት ወደ ሌላኛዉ ግዛት የሚደረግ ጉዞ ለሁለት ሳምንታት ተከለከለ፡፡መመሪያዉ በ36ቱ የሀገሪቱ ግዛቶች የሚተገበር ነዉ፡፡

~ በዩናይትድ ኪንግደም በኮሮና ቫይረስ የተነሳ ህይወታቸዉን ያጡ ሰዎች ቁጥር 18,738 ደረሰ፡፡

~ የጀርመን የቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎች ከ15 ቀናት በኃላ ሊመለሱ እንደሚችል የጀርመን እግር ኳስ የሊግ ጨዋታዎች ዋና ስራ አስፈጻሚ ክርስቲያን ሴፊርት ተናግረዋል፡፡ጨዋታዎቹ ያለ ደጋፊ የሚካሄዱ ሲሆን አስቀድሞ ግን የፖለቲከኞችን ዉሳኔ ይሻሉ፡፡

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 15፣2012-አሜሪካ በፐርሺያ ቀጠና የደህንነት ችግር የምትፈጥር ከሆነ የጦር መርከቦቿን ኢራን እንደምታወድም አስጠነቀቀች

አሜሪካ በፐርሺያ ቀጠና የደህንነት ችግር የምትፈጥር ከሆነ የጦር መርከቦቿን ኢራን እንደምታወድም አስጠነቀቀች

የኢራን ዋና ጄነራል ሆስኒ ሳላሚ እንደተገሩት በፐርሺያ ቀጠና የደህንነት ችግር አሜሪካ የምትፈጥር ከሆነ የኢራን የባህር ሀይል በአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ አስተላልፌለዉ ብለዋል፡፡

በትላንትናዉ እለት ዶናልድ ትራምፕ በፐርሺያ ባህረ ሰላጤ የኢራን መርከቦች ማንኛዉንም አይነት ትንኮሳ ካደረሱ የአሜሪካ የባህር ሀይል እርምጃ እንደሚወስድ መናገራቸዉ ይታወሳል፡፡

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 15፣2012-አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሸራ ወጥረው ህገ ወጥ- ቤት በመስራት 20 ሰዎችን በቤቱ ሰብስቦ ሺሻ ሲያስጨስ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማናቸውም ቦታ የሺሻ ማስጨስና የጫት ማስቃም አገልግሎት መስጠትን ይከለክላል፡፡ግለሰቡ ግን የአዋጁን ክልከላ በመጣስ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት የሚሆን ድርጊት ሲፈፅም እና ሲያስፈፅም ከ30 በላይ ከሚሆኑ የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች ጋር እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታዉቋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ጎማ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተለያዩ ሁለት ቦታዎች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሺሻ ሲያስጨሱ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ቲም ሀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እሱባለው ጌትነት ገልፀዋል፡፡ በሁለቱ መኖሪያ ቤቶች 15 ሰዎች ሺሻ ሲያጨሱ የተገኙ ሲሆን 66 የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች ተይዘዋል፡፡

ጦማር/ዜና

ሚያዝያ 15፣ 2012-በኢትዮጵያ በዛሬዉ እለት በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው አለመኖሩ ተረጋግጧል

ባለፉት 24 ሰዓት በ965 ሰዎች ላይ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በእለቱ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰዉ አለመኖሩ የጤና ሚንስትር ይፋ አድርጓል፡፡

ተጨማሪ መረጃ

~ አጠቃላይ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር 10‚736 ደርሷል።

~ በቫይረሱ መያዛቸዉ የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 116 ነዉ፡፡

~ በዛሬዉ እለት በቫይረሱ የተያዘ ሰዉ ሪፖርት አልተደረገም፡፡

~ አጠቃላይ ያገገሙ ግለሰቦች 21 ደርሰዋል።

~ በጽኑ ህሙማን ማከምያ ዉስጥ የሚገኝ ታማሚ የለም፡፡

~ በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ 90 ናቸው።

~ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።