መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 10፤2014-የፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትር ከእንግሊዝ አቻቸው ጋር የሚያደርጉትን ውይይት ሰረዙ

በእንግሊዝ፣አሜሪካ እና አውስትራሊያ መካከል የተደረሰው አዲስ የፀጥታ ስምምነት ፈረንሳይን አስቆጥቷል። አውስትራሊያ፣እንግሊዝና አሜሪካ የኒውክሌር ኃይል ያለውን ሰርጓጅ መርከብ ለመስራት የደረሱበት ስምምነት አስቀድሞ ፈረንሳይ ከአውስትራሊያ ጋር የነበራትን ውል የሚያስቀር በመሆኑ ፓሪስን አላስደሰተም።

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ስምምነቱ ፈረንሳይን ሊያሳስባት አይገባም ሲሉ ተናግረዋል።ሆኖም ግን የፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትር ፍሎረንስ ፓርሊ በዚህ ሳምንት ከእንግሊዝ አቻቸው ቤን ዋላስ ጋር የነበራቸው ውይይት ተሰርዟል።

በደቡባዊ ቻይና ባህር የቻይናን ተፅእኖ ለመቀነስ በማሰብ ባላፈው ሳምንት በአሜሪካ፣አውስትራሊያ እና እንግሊዝ መካከል ስምምነት መደረሱ ይታወሳል።ሆኖም ግን ፈረንሳይ ከአውስትራሊያ ጋር በ2016 የባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመገንባት 37 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውል ቢያስሩም አዲሱ ስምምነት ይህንን የሚያስቀር ሆኗል።

የፈረንሳይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኢቭስ ሌ ድሪያን በአጋሮቻችን የተደረገው ስምምነት ተቀባይነት የሌላው ከጀርባ እንደ መውጋት ነው ሲሉ ኮንነውታል።የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከዋሽንግተን እና ካንቤራ አምባሳደሮቻቸውን ጠርተዋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *