መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 20፤2016- በእንጦጦ ፓርክ ዙሪያ የውንብድና ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በ16 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ ፓርክ ዙሪያ የቅሚያ እና የውንብድና ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት መቀጣታቸዉን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከአዲስአበባ ፖሊስ ያገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

የጣቢያው የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ፍቅሩ ማሞ እንደገለጹት ዮናስ ዳኜና ለጊዜው ያልተያዘው ግብረአበሩ በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ቀናት በፓርኩ ዙሪያ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ የኃይል ተግባር በመጠቀም የቅሚያ እና የውንብድና ወንጀል በመፈፀም ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶችን ሲዘርፉ ቆይተዋል፡፡

ወንጀል ፈፃሚዎቹ ፍርድ ቤት ከቀረቡ እና የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መቅረታቸውንም አመላክተዋል፡፡

የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉለሌ ምድብ ችሎት ሁለቱም ተከሳሾች በተደጋጋሚ ቀጠሮ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው በሌሉበት እያንዳንዳቸው በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ፖሊስም ፍርደኞቹን አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት ለማስረከብ ባደረገው ጥረት ዮናስ ዳኜ የተባለው ግለሰብ ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉ እና ግብረአበሩን ለመያዝ  ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *