መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 12፤2016 –በአካል ጉዳት ምክንያት ለበርካታ ዓመታት ከትምህርት ገበታ ርቀው የቆዩት የ70 ዓመቱ አዛዉንት ትምህርታቸዉን ለመከታተል ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ

የ70 ዓመቱ አዛዉንት ትምህርታቸዉን ለመከታተል ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀላቸው ተሰምቷል።

የ10 ልጆች አባትና የልጅ ልጆችን ያዩት አቶ ዮሐንስ አዲሴ በ70 ዓመታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመማር ወደ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸዉን ብስራት ራዲዮና መለሎ ከዩኒቨርስቲው ያገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የ2016 ዓ.ም አዲስ ገቢ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን ትናንት መቀበል ጀምሯል፡፡

አቶ ዮሐንስም በ2015 ዓ.ም የተሰጠውን ሀገር አቀፍ ፈተና አልፈው ወደ ተመደቡበት ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ልዩ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በልጅነታቸው ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩና ባጋጠማቸው የአካል ጉዳት ምክንያት ለበርካታ ዓመታት ከትምህርት ገበታ ርቀው መቆታቸውንም በአቀባበሉ ላይ ተናግረዋል፡፡

ለትምህርት ካላቸው ፍላጎት አኳያም ያቋረጡትን ትምህርት በመቀጠል ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሀዲያ ዞን ዱና ወረዳ ለጠቦ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አዛውንቱ ተማሪ ከተማሩበት ትምህርት ቤት የ2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስደው ካለፉ ጥቂት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች አንዱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውንም በትጋት ለመከታተል በቂ ዝግጅት አድርጌያለሁም ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *