መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 12፤2016-ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ ወደ 400 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ሃማስ አስታወቀ

በጋዛ በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ተገድለዋል ብሏል። በአጠቃላይ 390 ሰዎች ሲሞቱ ተጨማሪ 734 ቆስለዋል ብሏል። ጦርነቱ ከጥቅምት 7 ጀምሮ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከ20,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

በጋዛ ሰርጥ ያለው ውጊያ የቀጠለ ሲሆን በእስራኤል የአየር ጥቃት ሰሜን እና ደቡባዊ የጋዛ ክፍል ክፉኛ ተጎድቷል። ሃማስ ወደ ደቡብ እና መካከለኛው እስራኤል ሮኬቶችን በመተኮሱ የተነሳ በትናንት እለት በቴል አቪቭ የሳይረን ድምፅ ሲሰማ ውሏል። የተባበሩት መንግስታት የአለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ሻዛ ሞግራቢ በጋዛ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ በመኖሩ ይህንን ለመከላከል አፋጣኝ ሰብአዊ የተኩስ አቁም እንደሚያስፈልግ በድጋሚ ገልፀዋል።

በአሁኑ ጊዜ በጋዛ ከሩብ በላይ የሚሆኑ አባወራዎች ለከፍተኛ ረሃብ የተጋለጡ መሆናቸውን  ቃል አቀባይ የሆነችው ሻዛ ሞግራቢ ተናግራለች። ከግብፅ ዕርዳታ ይዘው የሚመጡ መኪናዎች የተወሰነ ምግብ፣ ውሃ እና መድኃኒት ያደረሱ ቢሆንም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግን የምግብ መጠን ለግዛቱ ሕዝብ ከሚያስፈልገው 10 በመቶው ብቻ ነው ብሏል።

ሃማስ እና ሌሎች የፍልስጤም ቡድኖች እስራኤል ጦርነቱን ለማቆም እስካልተስማማች ድረስ ተጨማሪ ታጋቾችን ለመልቀቅ ስምምነት ላይ እንደማይደርሱ በመግለፃቸው የተኩስ አቁም ተስፋ መና ቀርቷል። የእስራኤል መንግስት ከሃማስ ጋር ቋሚ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነትን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።

በሚሊዮን ሙሴ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *